ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጥራት ያለው የሙዝ ምርት ከሀገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ገበያ እየቀረበ ነው

አርባ ምንጭ፤ ሕዳር 1/2019 (ኢዜአ) ፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጥራት ያለው የሙዝ ምርት ከሀገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅርብ ገቢን ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የገበያ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ድጋፍ ክትትልና አስተዳደር ዳይሬክተር አስናቀ ለገሠ እንደገለጹት፣ በክልሉ ሙዝን በስፋትና በጥራት በማምረት ከልማቱ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

በዚህም ክልሉ ምርቱን ከሀገር ውስጥ ባለፈ ወደውጭ በመላክ ለውጭ ምንዛሬ ገቢ ማደግ የራሱን አስተዋጾ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ቢሮው ህጋዊና ዘመናዊ የንግድ ሥርአትን በመዘርጋት የአምራቹን፣ የሸማቹንና የንግዱን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ላመሳደግ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም አመለክተዋል።


 

በክልሉ በጋሞ፣ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ እና አሪ ዞኖች ሙዝ በስፋት እንደሚመረት የገለጹት አቶ እስናቀ፣ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ከ50 ሺህ ቶን በላይ ሙዝ ለገበያ መቅረቡንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 886 ቶን ሙዝ ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ከ6 ሚሊዮን 644 ሺህ ዶላር በላይ ግብይት መፈጸሙን አስታውቀዋል።


 

ምርቱን በወቅቱ ለገበያ ለማድረስ በሚደረግ ጥረት በግብይት ስርዓት ውስጥ ማነቆ የሆኑ ህገ ወጥ ደላሎችና ኬላዎችን ለመቆጣጠርም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከሙዝ አምራች አርሶ አደሮች መካከል በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ሼሌ ሜላ ቀበሌ ነዋሪ ማርቆስ ኬቾ እና ዲዶ ጳኮ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት የሙዝ ምርት ለአካባቢው ትልቅ የኢኮኖሚ ምንጭ ነው።

ሙዝን በስፋት በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት አምራቾቹ፣ ከልማቱ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እንቅፋት ለሆኑ ህገወጥ ደላሎች መንግስት መፍትሄ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

በሙዝ ንግድ ሥራ ከተሰማሩት መካከል የጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ ላሃ ከተማ ነዋሪ አቶ ሳሙኤል ፈይሳ የሙዝ ምርትን ከአምራቹ በቀጥታ ገዝተው ለተለያዩ ከተሞች እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።

ይበልጥ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለገበያ እንዲቀርብም አምራቹን ማደራጀትና ግንዛቤውን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሚመለከተው የመንግስት አካል ለግብይት ሥርአቱ እንቅፋት የሆኑ አሰራሮችና ህገ-ወጥ ኬላዎችን በማስወገድ የበኩሉን እንዲወጣም አመለክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም