ኢትዮጵያ የስደት አስተዳደርን በብሔራዊ ቅድሚያ ጉዳይነት በመያዝ ተቋማዊ አቅሟን እያጠናከረች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የስደት አስተዳደርን በብሔራዊ ቅድሚያ ጉዳይነት በመያዝ ተቋማዊ አቅሟን እያጠናከረች ነው
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 1/2019 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ የስደት አስተዳደርን በብሔራዊ ቅድሚያ ጉዳይነት በመያዝ ተቋማዊ አቅሟን እያጠናከረች መሆኑን የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ይህንን ያስታወቀው የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (IOM) እና የኔዘርላንድ መንግስት የኮምፓስ (COMPAS) ፕሮግራም 5ኛ ዓመት ትግበራ መርሃ-ግብር ላይ ነው።
በህገ-ወጥ ስደት መከላከል እና በተመላሽ ዜጎች ድጋፍ ረገድ በኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (IOM) ትብብር ከፍተኛ ውጤት ማምጣቱ ተመላክቷል።
በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህገወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል እና የተመላሽ ዜጎች ጉዳይ መሪ ስራ አስፈጻሚ ደረጀ ተግይበሉ፤ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፣ አስተዋጽኦው ብሔራዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለማሳካት መደገፉን ገልጸዋል።
አጋርነቱ በፕሮግራም ተግባራት ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን ብሔራዊ ተቋማትን፣ ፖሊሲዎችን፣ የቅንጅት ሥርዓቶችንና ዘላቂ መዋቅሮችን በማጠናከር ላይ ያተኮረ ነበር ብለዋል።
በመንግሥት አመራር ሥር የተዋቀረ ትብብር ለማካሄድ የሚያስችል የትብብር ስምምነት መዘጋጀቱ እንደ አንድ ዋና ምዕራፍ ተጠቅሷል ብለዋል።
ይህ ስምምነት ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ስትራቴጂያዊ ትብብር፣ ተቋማዊ አጋርነት፣ ተጠያቂነትና ዘላቂነትን ለማረጋገጥ የአምስት ዓመት ዕቅድ ከማዘጋጀት ጋር መያያዙንም ተናግረዋል፡፡
በፕሮግራሙ አማካኝነት በሰዎች የመገበያየት ወንጀል ሰለባዎችን የመለየት የተቀናጀ አካሄድ ማደጉ እና ብሔራዊ የመገናኛ ስትራቴጂ መጀመሩ እንደ ስኬት ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡
የዓለም አቀፉ ፍልሰት ድርጅት (IOM) የኢትዮጵያ ሚሲዮን ኃላፊ አቢባቱ ዋኔ የኮምፓስ (COMPAS) የአምስት ዓመት ጉዞ ዘላቂ ትብብርና የጋራ ኃላፊነት ያለውን ጠቀሜታ ማሳየቱን ገልጸዋል።
ፕሮግራሙ ደኅንነቱ የተጠበቀና ሕጋዊ ስደትን ለማበረታታት፣ የስደተኞችን ጥበቃ ለማጠናከር እንዲሁም ከፌዴራል እስከ ክልል፣ ከሲቪል ማኅበራትና ከማኅበረሰቦች ጋር በቅርበት ለመሥራት ዕድል መፍጠሩን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ አምባሳደር ክሪስቲን ፒሬኔ በኔዘርላንድ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄደው ይህ ፕሮግራም በ14 ሀገራት ውስጥ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኮምፓስ (COMPAS) ፕሮግራም የሁለቱን ሀገራት የስደት ጉዳይ በአንድ የተቀናጀ ማዕቀፍ ውስጥ በማካተት በኢትዮጵያና በኔዘርላንድ መካከል ያለውን ጠንካራ ትብብር ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ጠቁመዋል።