ቀጥታ፡

ዓለም አቀፍ የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት ነገ በሳይንስ ሙዚየም ይከፈታል

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 1/2019 (ኢዜአ) ፦ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ13ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት ነገ በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም ተከፍቶ በመላው ሀገሪቱ እንደሚከበር የኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሺፕ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኩነቱን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በኢንተርፕረነርሺፕ ዘርፍ ከሚሠራው "ድሪም ቪሲ" ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በጋራ እንዳዘጋጀው ሁነቱን በማስመልከት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተመላክቷል።

ድሪም ቪሲ ዋና መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ለንደን ያደረገ ሲሆን፣ በአፍሪካ የቴክኖሎጂ እና የስታርትአፕ ንግድ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው።


 

ድርጅቱ በአፍሪካ የኢንቨስትመንት ማኅበረሰብ ውስጥ አዳዲስ ባለሙያዎችን በመቅረጽ እና የእውቀት ሽግግር እንዲደረግ በማድረግ የአህጉሪቱን የስታርትአፕ ሥነ-ምህዳር ለማጠናከር ይሠራል።

በኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሺፕ ኢንስቲትዩት የኢንተርፕረነርሺፕ ሥነ-ምህዳር ግንባታ ዳይሬክተር አቶ ዱጋሳ ተሰማ በበኩላቸው፤ ሁነቱ አዳዲስ ሥራ ፈጣሪዎች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ መነሳሳትን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም መድረኩ ሥራ ፈጣሪዎች እርስ በእርስ የሚገናኙበትና ልምድ የሚለዋወጡበት እንደሚሆን ጠቁመው፤ በሁነቱ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት፣ ከፖሊሲ አውጪዎች፣ ከትምህርት ተቋማት እና ከሕግ አውጪዎች ጋር ሰፊ ውይይቶች እንደሚደረጉ ተናግረዋል።

አክለውም ኢንስቲትዩቱ የግለሰቦችንና የተቋማትን አቅም በመገንባት፣ ከመንግሥትና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ተገቢውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የድሪም ቪሲ ተባባሪ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሲምዲ ኤይ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የተደረገው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡


 

ሁነቱ ዓለም አቀፍ ካፒታልን ወደ ሀገር ውስጥ ከመሳብ ባለፈ በዓለም አቀፍ ባለሀብቶችና በሀገር ውስጥ ኩባንያዎች መካከል የእውቀትና የንግድ ልውውጥ ለመፍጠር እንደሚረዳ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም