የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክን በዘላቂነት ለማልማትና ለመጠበቅ የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብርን ማጠናከር ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክን በዘላቂነት ለማልማትና ለመጠበቅ የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብርን ማጠናከር ያስፈልጋል
ጋምቤላ ፤ህዳር 1/2019 (ኢዜአ) ፦የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክን በዘላቂነት ለማልማትና ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።
አፍሪካን ፓርክስ ኔትዎርክ የፓርኩን ጥበቃ ለማጠናክር 48 አዲስ የሬንጀር አባላትን አሰልጥኖ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ በማስመረቅ ወደ ስራ አሰማርቷል።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ተወካይ ፋኑኤል ከበደ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክን በማልማትና በመጠበቅ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ልማት ለማዋል በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ጥረት ያስፈልጋል ።
ብሔራዊ ፓርኩን ከአፍሪካን ፓርክስ ኔትዎርክ ጋር በመቀናጀት በዘላቂነት በማልማት ሀብቱን ጥቅም ላይ ለማዋል ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የፓርኩ ብዝሃ ህይወት ተጠብቆ በዘላቂነት ጥቅም ላይ እንዲውል የጥበቃ ስራዎችን ማጠናከር መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም የጥበቃ ባለሞያዎችን በየግዜው በማፍራት ወደ ብሔራዊ ፓርኩ ማሰማራቱን አመልክተዋል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከአፍሪካን ፓርክስ ኔት ወርክ ጋር በመቀናጀት ሀብቱን በማልማትና በመጠበቅ ለዘላቂ የቱሪዝም ልማት ለማዋል የጀመራቸውን ስራዎች አጠናከሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ብርሃኑ አሰፋ በበኩላቸው የአፍሪካ ፓርክስ ኔትዎርክ ፓርኩን በተረከበ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በርካታ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስት ፓርኩን በዘላቂነት ለማልማት ለተጀመሩ ስራዎች መሳካት ሁለንተናዊ ድጋፍና ትብብሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የዕለቱ ተመራቂዎች የፓርኩን ብዝሃ ህይወት በመጠበቅ ረገድ ኃላፊነታቸውን በትጋት እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
የአፍሪካን ፓርክስ ኔትዎርክ ዋና ኦፕሬሽናል ኦፊሰር ሚስተር ቻርልስ ዊልስ በወቅቱ እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግስት ለተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ።
ለዚህም ማሳያው የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ በአፍሪካን ፓርክስ ኔትዎርክ በዘላቂነት እንዲለማ የወሰደው እርምጃ ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል።
የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ልዩ የተፈጥሮ ገጽታ ያለውና ለቱሪዝም ልማት ምቹ መሆኑን ጠቁመው በፓርኩ ለተጀመሩ የልማትና የጥበቃ ስራዎች መሳካት የሁሉም ድጋፍና ትብብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የዕለቱ ተመራቂዎች ለሁለት ወር የተግባርና የንድፈ ሃሰብ ስልጠና የወሰዱ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በአፍሪካ ፓርክስ ኔትወርክ የጋምቤላ ብሄራዊ ፓርክ ስራ አስኪያጅ አቶ ሀብተየሱስ ማቴዎስ ናቸው።
የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ በውስጡ 69 የአጥቢ ፣323 የአእዋፍ፣ 493 የዕፅዋትና ሌሎች የብዝሃ ህይወት ሀብቶች ይገኙበታል።