ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛነቷ የዓለም አቀፍ ሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎች ቀዳሚ መዳረሻ አድርጓታል

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 1/2019 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛነቷና የጥንታውያን ቅሪተ አካላት ባለቤት መሆኗ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎች ቀዳሚ መዳረሻ እንዳደረጋት የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ገለጹ።

ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ እና የረጅም ዘመናት አኩሪ ታሪክ ባለቤት የሆነች ድንቅ የሥልጣኔ ምድር ናት።

ይህ ህያው ሀገራዊ እውነታ እና ልዩ ልዩ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ ቅርሶቿ የዓለምን ትኩረት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲስብ አድርገዋል።

የመደመር መንግሥትም ይህንን ታላቅ ሀብት መነሻ በማድረግ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የታሪክና የሥልጣኔ ከፍታ የሚያሸጋግሩ ስልታዊ ሥራዎችን በቁርጠኝነት በመተግበር ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ኢትዮጵያ ወደ ኋላ 4 ሺህ 300 ዓመታት ገደማ የሚሻገር የሥልጣኔ ታሪክ አላት።

አክሱም፣ ላሊበላ፣ ፋሲለደስ፣ ጁጎል ግንብ፣ የጅማ አባ ጅፋር ቤተ መንግሥትና ሌሎችም ቅርሶች ኢትዮጵያ ረጅም የሀገረ መንግሥት ታሪክ ያላት መሆኗን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ በዋናነት የምትታወቀው በሰው ዘር መገኛነቷ እንደሆነም አብራርተዋል።

አሁን ሳይንስ በደረሰበት ደረጃ በዓለም ላይ 23 የሰው ልጅ ዝርያን የሚያሳዩ ቅሪተ አካላት የሚገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 14ቱ በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

እነዚህ 14 ቅሪተ አካላት በተለያዩ ዘመናት ላይ የተገኙ መሆናቸው ልዩ እንደሚያደርገውም አስረድተዋል።

በዚህም በርካታ ተመራማሪዎች በዘርፉ ምርምር ለማካሄድ ኢትዮጵያን ተመራጭ  ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የራሳቸው ባህልና እሴት ያላቸው የተለያዩ ብሔረሰቦች መኖሪያ መሆኗን ጠቅሰው፤ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች የታደለች ሀገር መሆኗን አብራርተዋል።

ባለሥልጣኑ ኢትዮጵያ በሰው ዘር መገኛነቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ቀዳሚነት ለማስጠበቅ በመካከለኛውና በታችኛው አዋሽ፣ በታችኛው ኦሞ ሸለቆና በሌሎች በተመረጡ ቦታዎች ላይ ምርምር እያካሄደ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የቅሪተ አካል ምርምር አቅም በሰው ኃይልም ሆነ በመሣሪያ የጎለበተ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ እና  በዩኔስኮ ተመዝግበው የሚገኙ ዓለም አቀፍ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን በስፋት ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱ ተናግረዋል።

ለዚህም በኤግዚቢሽን፣ በሕትመት እንዲሁም ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ዓለም አቀፍ ቅርሶች የሚጎበኙበትን አሠራር ለመፍጠር እንደሚሙመቻች አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም