ቀጥታ፡

ከአንታሊያ እስከ አዲስ አበባ

(በሙሴ መለሰ)

የአየር ንብረት ለውጥ በዓለማችን ህልውና ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ እየበረታ በመጣበት በአሁኑ ወቅት፣ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በተለይም አፍሪካ ፍትሃዊ ምላሽ ለማግኘት የሚያደርጉት ትግል ተጠናክሮ ቀጥሏል።

አህጉሪቷ ለዓለም አቀፉ በካይ ጋዝ ልቀት ያላት ድርሻ አነስተኛ ቢሆንም፣ የችግሩ ቀዳሚ ገፈት ቀማሽ በመሆን ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለች ትገኛለች።

ይህንን ታሪካዊ ኢፍትሃዊነት ለመቀልበስ እና የአየር ንብረት ድርድሩን ከተበዳይነት ስሜት ወደ መፍትሔ አቅራቢነት ለማሸጋገር፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ መድረክ ላይ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ሚና እና ሀገር በቀል የአካባቢ ጥበቃ ስራዎቿን በማስተሳሰር ግንባር ቀደም ስትራቴጂካዊ መሪነቷን እያሳየች ነው።

ይህ የአፍሪካ የጋራ ድምፅ እና የፍትህ ጥያቄ በአሁኑ ወቅት በቱርኪዬ አንታሊያ ከተማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው 31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ በጎላ ሁኔታ እየተሰማ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በዚሁ ጉባኤ ላይ ጠንካራ ተሳትፎ እያደረገች ትገኛለች ።

ኢትዮጵያ በኮፕ 31 ጉባኤ ብሔራዊ ፓቪሊዮኗን የከፈተች ሲሆን ይህ መድረክ የሀገሪቱን የአረንጓዴ ልማት ስኬቶች ለዓለም ለማስተዋወቅ ታላቅ አጋጣሚ ፈጥሯል።

ከአንታሊያ ተጀምሮ ወደ አፍሪካ መዲና የሚዘልቀው ይህ ጉዞ፣ እ.አ.አ በ2027 በአዲስ አበባ ለሚስተናገደው ታሪካዊው የኮፕ 32 ጠንካራ መሠረት የመጣያ ስልታዊ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) ላይ ባደረጉት ንግግር ባነሷቸው ሀሳቦች በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃ ብቻውን ተነጥሎ የሚታይ ሳይሆን የአገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አካል ነው ያሉ ሲሆን የኢትዮጵያ 90 በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከውሃ የሚመንጭ መሆኑን እና ይህን ንጹህ ኃይል ለጎረቤት ሀገራትም ጭምር ታቀርባለች ብለዋል።

ሀገሪቱ በአንታሊያ እያደረገችው ያለው ተሳትፎ በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የሚመራ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዚዳንት የሆኑት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ዋና ተደራዳሪ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በስፍራው ተገኝተዋል።

ልዑካን ቡድኑ የጉባኤው አስተናጋጅ ከሆነችው ቱርኪዬ እና የኮፕ የድርድር ሊቀ መንበር አውስትራሊያ ጋር በቅርበት በመሥራት ላይ ነው።

ዓላማውም በአየር ንብረት ድርድር ላይ የዳበረ ልምድ ማግኘት፣ ተደራሽነቷን ማስፋት እና የኮፕ 32 አስተናጋጅነቷን ኃላፊነት በተሳካ ሁኔታ ለመረከብ የሚያስችላትን የሽግግር ዝግጅት ማፋጠን ነው።

የአንታሊያው ጉባኤ በተለይም በማደግ ላይ ለሚገኙ የዓለም ሀገራት እና ለአፍሪካ ወሳኝ በሆኑት እንደ የአየር ንብረት ፋይናንስ፣ የዝግጁነት አቅም ማጠናከር እና የልቀት ቅነሳ ቃል ኪዳኖች ዙሪያ ከፍተኛ ውይይት እየተካሄደበት ይገኛል።

ኢትዮጵያ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ከአፍሪካ የድርድር ቡድን (AGN)፣ በማደግ ላይ ከሚገኙ ሀገራት እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመሆን የጋራ አቋሞችን ለመቅረጽ እየሠራች ትገኛለች።

ይህ ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ያደጉ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መቋቋሚያ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ እንዲሰጡ ግፊት ከመፍጠር ባለፈ በአንታሊያ የሚደረጉ ስምምነቶች ለአዲስ አበባው ጉባኤ ስኬት ስንቅ እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመም ነው።

ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው የኮፕ 32 የዝግጅት ጉዞ በከፍተኛ ሀገራዊ ቁርጠኝነት እና በተግባራዊ እቅድ እየተከናወነም ይገኛል።

የዓለማችን ግዙፍ ዓመታዊ የአየር ንብረት ጉባኤ የሆነውን ይህንን ኩነት በብቃት ለማስተናገድ ኢትዮጵያ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን የጀመረች ሲሆን፣ በተለይም እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ ሀገር በቀል ስኬቶቿን ዓለም አቀፍ ማሳያ ለማድረግ እየተሰራም ይገኛል።

በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ የዓለም መሪዎችን እና ልዑካንን በብቃት ለመቀበል በአዲስ አበባ ታላቅ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

ይህም የሰው ዘር መገኛ የሆነቸው ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ለአየር ንብረት ፍትህና ዘላቂ መፍትሔ የጋራ የድርጊት አቅጣጫ የሚቀመጥበት ታሪካዊ እድል እውን ያደርጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም