የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ለተቋማዊ እድገትና አዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ለተቋማዊ እድገትና አዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 1/2019 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ለተቋማዊ እድገት፣ የኢንሹራንስ አገልግሎትንና አዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዳግማዊት ሽፈራው ገለፁ።
የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ነዋዮች ገበያ የአዋሽ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማህበር የምዝገባ፣ የእውቅና መስጠት እና የግብይት መክፈቻ መርሃ ግብር አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዳግማዊት ሽፈራው በዚሁ ጊዜ፤ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት አቅም ያላቸው በመሆናቸው የኢንቨስትመንት አማራጮቻቸው ሊሰፉ ይገባል ብለዋል፡፡
አዋሽ ኢንሹራንስ በካፒታል ገበያው የተመዘገበ የመጀመሪያው የኢንሹራንስ ኩባንያ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ ጠቅሰዋል፡፡
ይህም የካፒታል አቅርቦትን ለማሳደግ፣ የገበያውን እንቅስቃሴ ለማጠናከር፣ ባለ አክሲዮኖች በሁለተኛ ደረጃ ገበያ ዋጋ ወጥቶላቸው እንዲገበያዩ ለማስቻል እንዲሁም በዘርፉ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ነዋይ ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዮዲት ካሳ በበኩላቸው፤ አዋሽ ኢንሹራንስ ወደ ገበያው በመቀላቀል ስምንተኛው መሆኑን ጠቅሰው የኢንሹራንስ ዘርፉን በመወከል ደግሞ የመጀመሪያው ኩባንያ መሆኑን ገልጸዋል።
የአዋሽ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ጂባት አለምነህ ኩባንያቸው አዳዲስ ለውጦችን በመቀበል ግንባር ቀደም መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በካፒታል ገበያው መመዝገቡ የእድገት ጉዟቸውን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግርና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ለተቋማዊ እድገት፣ ለኢንሹራንስ አገልግሎቶች መስፋፋት እና ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት አዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚፈጥር ታላቅ መድረክ መሆኑ ጠቁመዋል፡፡