የአሸናፊዎች ምድር- ኢትዮጵያ - ኢዜአ አማርኛ
የአሸናፊዎች ምድር- ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ ከቀደምት ታሪካዊ ሥልጣኔዎቿ ጎን ለጎን በስፖርቱም ዘርፍ ቀደምት ከሆኑ ሀገራት መካከል ትጠቀሳለች። ኢትዮጵያ በእውነትም የጀግኖች፣ የድል እና የታላቅ ታሪክ ባለቤት የሆነች የአሸናፊዎች ምድርም ናት። ኢትዮጵያ በስፖርት ዘርፍ ዓለምን ያስገረሙ በርካታ ድሎችን ያስመዘገበችና እያስመዘገበች የምትገኝ ሀገር ናት።
በስፖርቱ ዓለም ኢትዮጵያ ያፈራቻቸው ጀግኖች አትሌቶች ባስመዘገቧቸው ድሎች የሀገራችንን ስም አስጠርተዋል፡፡ ሻምበል አበበ በቂላ እጅግ ድንቅ በሆነ ታሪክ በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ ማራቶንን በማሸነፍ ለጥቁር ሕዝቦች የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በማጎናጸፍ ታሪክ የሰራ ጀግና አትሌት ነው።
አትሌት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በባርሴሎና ኦሎምፒክ በ10 ሺህ ሜትር በማሸነፍ ለአፍሪካ ሴቶች ድል መቀዳጀት እንደሚቻል አሳይታለች። በአትላንታ ኦሎምፒክ ደግሞ አትሌት ኮማንደር ፋጡማ ሮባ በ42 ኪሎ ሜትር ማራቶን በማሸነፍ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ ሴት የማራቶን አሸናፊ በመሆን ለሴቶች አሸናፊነት ምሳሌ የሆነች እንቁ አትሌት ነች። እነ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ አትሌት ኮማንደር ጥሩነሽ ዲባባ፣ አትሌት ረዳት ኮሚሽነር ቀነኒሳ በቀለ፣ አትሌት ኮሎኔል መሰረት ደፋር እና ሌሎችም አትሌቶች ኢትዮጵያ የአሸናፊዎች ምድር መሆኗን በተደጋጋሚ ለዓለም አሳይተዋል።
በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የአሸናፊነት ሰንደቃችንን ከፍ አድርገው ያወለበለቡና የረጅም ርቀት ንጉሥ መሆናችንን ያስመሰከሩ ታላላቅ ስሞች ይህች በታሪክ የበለጸገች እና የድል ባለቤት የሆነች ሀገር አሁንም አሸናፊነቷን እያስቀጠሉ ይገኛሉ።
በእግር ኳስም ቢሆን ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መሥራች ሀገራት መካከል አንዷ ብቻ ሳትሆን፣ የአፍሪካ ዋንጫ በማዘጋጀት ዛሬ አህጉራዊው ውድድር ለደረሰበት ትልቅ ደረጃ መሠረት የጣለች ታሪካዊ ሀገር ናት።
ኢትዮጵያ ከሌሎች ጋር በመሆን የአፍሪካ ዋንጫን በመመሥረትና በማዘጋጀት አፍሪካውያን በራሳቸው መሬት ውድድር እንዲያካሂዱና እርስ በእርስ ግንኙነታቸውን እንዲያጠናክሩ ትልቅ ሚና ተጫውታለች። ኢትዮጵያ 3ተኛውን የአፍሪካ ዋንጫን ስታስተናግድም ግብጽን 4ለ2 አሸንፋ የዋንጫ ባለቤት በመሆን የአሸናፊ ሀገርነቷንም አስመስክራለች።
ኢትዮጵያ የዘለቀና የገዘፈ የእግር ኳስ ተሳትፎ የነበራት ሀገር ብትሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን ተሳትፎዋና ውጤታማነቷ እየቀነሰ መምጣቱ ይታወቃል። በእግር ኳሱ ዘርፍ ከነበራት ቀዳሚነት ጋር አብራ ማደግና መዘመን ሳትችል በመቅረቷ ወደ ኋላ ለመንሸራተት ተገዳለች።
ይህም የእግር ኳስ ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጭት ሆነ፤ ዛሬም 'መቼ ይሆን የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ትንሣኤ?' እንዲል እያደረገው ይገኛል። ይህ ሁኔታ ያስቆጨው የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያ የነበራትን ቀዳሚነትና ከፍታ ለመመለስ አሸናፊ የእግር ኳስ ቡድን ለመገንባት ሰንቆ ተግባራቱን ማከናወን ከጀመረ ውሎ አድሯል።
ከእነዚህ ጥረቶች መካከልም ሀገሪቱ ለረጅም ዓመታት የራቀችበትን የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከ51 ዓመታት በኋላ በድጋሚ በማስተናገድ እግር ኳሱን ማነቃቃት እንዲሁም ውጤታማና አሸናፊ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት የጀመረችውን ጉዞ ማንሳት ይቻላል።
ይህንን ተከትሎ መንግስት ውድድሩን ለማስተናገድ መሠረታዊ የሆኑ ስታዲየሞችን መገንባትና ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ማድረግን ጨምሮ በርካታ ውጤታማ ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛሉ። ለአብነት ያህል ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው በመገንባት ላይ የሚገኙት ግዙፎቹ የባሕር ዳር እና የአደይ አበባ ዓለም አቀፍ ስታዲየሞች ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲጠናቀቁ እየተደረገ ይገኛል።
በተጨማሪም የጅማ እና የድሬዳዋ ስታዲየሞች ግንባታና ጥገና፣ እንዲሁም የቃሊቲ፣ የአበበ ቢቂላ እና የአዲስ አበባ ስታዲየሞች እድሳት ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ዘመናዊ ስታዲየሞች ኢትዮጵያ ታላላቅ አህጉራዊ ውድድሮችን በተለይም የአፍሪካ ዋንጫን በድጋሚ እንድታዘጋጅ ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ እና ጠንካራ መሠረት እንዲጣል ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረጉ ይገኛሉ።
የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገድ ጥያቄ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የ2029ኙን የአፍሪካ ዋንጫ እንድታዘጋጅ 46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ባካሄደበት ወቅት ለካፍ መደበኛ ጉባኤ የመጡ የአፍሪካ እግር ኳስ የበላይ አመራሮችና ተሳታፊዎች በተገኙበት በቤተ መንግሥት በተደረገው የራት ግብዣ ላይ ይፋዊ ጥያቄ ማቅረባቸው አይዘነጋም።
ሀገሪቱ የተለያዩ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ ሪፎርሞች እያካሄደች መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን ላይ በስፖርቱ በተለይም በእግር ኳስ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የመሠረተ ልማት ማሻሻያ እና ተያያዥ የለውጥ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ለካፍ ከፍተኛ አመራሮች ገልጸዋል።
በዚሁ የራት ግብዣ ላይ የተገኙት የቀድሞ የአህጉራችን ታላላቅ የኳስ ኮከቦች ሳሙኤል ኤቶ፣ አልሃጅ ዲዮፍ፣ ጄጄ ኦኮቻ እና የመሳሰሉት ኢትዮጵያ ዋንጫውን የማዘጋጀት ሙሉ አቅም እንዳላት የሚያሳዩ አዎንታዊ ሁኔታዎችን መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የማስተናገድ ጥያቄን ተከትሎ የአፍሪካ ዋንጫን ቤቱ ለመመለስ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የስታዲየም ግንባታዎችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ የቤት ሥራዋን በቁርጠኝነት በማጠናቀቅ ላይ ትገኛለች።
የአፍሪካ ዋንጫን ወደ ቤቱ መመለስ
ኢትዮጵያ አፍሪካ ዋንጫን ዳግም ወደ ሀገሯ ለመመለስ ጥያቄ አቅርባ ምላሽ ማግኘቷን ተከትሎ፣ ውድድሩን ለአራተኛ ጊዜ ለማሰናዳት በዝግጅት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ የካፍ (የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን) ገምጋሚ ቡድን ጥብቅ ፍተሻ ሲያደረግባት ቆይቷል።
ውድድሩን ካስተናገደች ግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረችው ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካ ዋንጫ ማስተናገጃነት ያቀረበቻቸው ዘመናዊ ስታዲየሞች ፍተሻ ተደርጎባቸዋል።
በአዲስ አበባ መቀመጫቸውን በሸራተን አዲስ ያደረጉት የካፍ ተወካዮች እና ገለልተኛ ገምጋሚ ቡድኖች፣ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በአካል በመገኘት ሰፊ ምልከታ አድርገዋል።
ቡድኑ በጉብኝቱ ወቅት ስታዲየሞችን ብቻ ሳይሆን የልምምድ ሜዳዎችን፣ የሆቴል መስተንግዶዎችን፣ የጤና ተቋማትን (ሆስፒታሎችን) እንዲሁም አጠቃላይ የከተሞቹን መሠረተ ልማት በጥልቀት ሲፈትሹ ሰንብተዋል።
በዚህ ጥልቅ ምዘና ውስጥ አደይ አበባ ስታዲየም፣ አዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ስታዲየም፣ ባህር ዳር ስታዲየም፣ ጂማ ስታዲየም፣ ድሬዳዋ ስታዲየም እና ሃዋሳ ስታዲየም ፍተሻ የተደረገባቸው ስታዲየሞች ናቸው።
በፍተሻው ሂደት መሠረት ኢትዮጵያ 37ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በባለቤትነት ለማዘጋጀት ትልቅ ተስፋ እንዳላት ገምጋሚዎቹ ግምገማ አመላካች ሆኗል። የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ቤቱ ሊመለስ መንገዱን ጀምሯል።
የአፍሪካ ዋንጫ ትሩፋት
ታላላቅ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮችን በሀገር ውስጥ ማስተናገድ ከስፖርታዊ ፋይዳው ባሻገር ለሀገር ገጽታ ግንባታ እና ለኢኮኖሚ እድገት ያላቸው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው።
ትልልቅ ውድድሮች በሀገር ውስጥ ሲካሄዱ የሚመጡ ስፖርተኞች፣ የውድድሩ ታዳሚዎች፣ ደጋፊዎች እና ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች ፍሰት የሆቴልና መስተንግዶ፣ የትራንስፖርት፣ የቱሪዝም፣ የአቪዬሽን እና ሌሎች ተያያዥ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን በቀጥታ በማንቀሳቀስ ለሀገር ውስጥ ገቢ ማደግ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።
እንዲሁም ዝግጅቱን በስኬት ማዘጋጀት የአገረቱን መስተንግዶ እና አጠቃላይ ገጽታ ለዓለም ማሳያ በመሆን ነገ ኢትዮጵያ ሌሎች ተጨማሪ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮችና መድረኮችን እንድታስተናግድ ሰፊ ዕድል ይከፍታል።
ከዚህ በላይ ደግሞ በሀገር ውስጥ የሚደረጉ አህጉራዊ ውድድሮች ዘመናዊ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን እንዲስፋፉ ከማድረጉም በላይ፣ ጠንካራ፣ ታላቅና አሸናፊ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ለሚደረገው ሥራ እና ለወጣት ትውልድ መነቃቃት ጥሩ መሠረት ይጥላል።