ቀጥታ፡

ባለሀብቶች የግብርና ምርቶችን እሴት ጨምረው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ ነው  

ሀዋሳ፣ ሕዳር1/2019(ኢዜአ)፡-የግብርና ምርቶችን እሴት ጨምረው ለውጭ ገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ገለጹ።

ባለሀብቶች የግብርና ምርቶችን በጥሬ ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምሮ መላክ ለውጭ ምንዛሬ ግኝትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።

በአቮካዶና ማር ማቀነባበር ሥራ የተሰማራው "ጎልደን አቮካዶ ካምፓኒ" ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ይርጋለም አስፋው እንዳሉት ድርጅታቸው የአቮካዶ እና የማር ምርትን እሴት ጨምሮ ወደ አውሮፓ ይልካል።

በተለይ በድፍድፍ መልክ የሚያዘጋጀውን የአቮካዶ ምርት ሙሉ በሙሉ በማቀነባበር የተጣራ ዘይት ለማምረት የሚያስችል ኢንዱስትሪ ለማቋቋምም ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በቂ የአቮካዶ ምርት እንዲኖር በግብርና ኢንቨስትመንት መሬት ተቀብለው አቮካዶ የማልማት ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ድርጅታቸው ከአቮካዶ ድፍድፍ በተጨማሪ ማርን በማቀነባበር ለገበያ እያቀረበ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ይርጋለም፣ ከ400 ለሚበልጡ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ገልጸዋል።

የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር እሴት ጨምሮ መላክ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ካለው ጠቀሜታ ባለፈ  ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።


 

በቡና ማቀነባበር ሥራ የተሰማራው "ሜሚ አግሮ ኢንዱስትሪ" ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ታረቀኝ በበኩላቸው በማቀነባበር እሴት የተጨመረበት ቡና ለውጪ ገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢንዱስትሪው በቡና ልማት ከተሰማሩ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ተረክቦ በራሱ የማበጠሪያ ኢንዱስትሪ አዘጋጅቶና እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል። 

ኢንዱስትሪው ከይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ መሰረተ ልማት የተሟላለት ቦታ መረከቡን የገለጹት አቶ ሲሳይ፣ እስካሁንም ከ300 ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

በሥራቸው ውጤታማ ለመሆንም ከክልሉ መንግስት ተገቢውን ድጋፍና እገዛ እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስልጤና ሀላባ ዞኖች በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማራው "ሎባ ጃብር ጥምር እርሻ ድርጅት" ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሽታ መሀመድ፣ በውጪ ምንዛሬ ከውጭ የሚገባን ቺያ ሲድ ምርት በሀገር ውስጥ አምርተው ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ምርቱ በአብዛኛው ከአሜሪካ እና ከኤሲያ ሀገራት ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገባ የተናገሩት ሥራ አስኪያጇ፣ ይህን በሀገር ውስጥ በማምረት ለመተካት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለዚህም በስልጤና ሃላባ ዞኖች በ18 ሄክታር መሬት ላይ ምርቱን ከማምረት ባለፈ እሴት ጨምረው ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን አስረድተዋል። 

በቀጣይም ምርቱን በጥራትና በብዛት በማምረት ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።


 

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት የግብርና ምርቶችን እሴት ጨምሮ ለውጪ ገበያ ማቅረብ እንደሀገር ልዩ ትኩረት የተሰጠው ነው፡፡

ምርቶችን እሴት ጨምሮ መላክ ለውጭ ምንዛሬ ግኝትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለዚህም መንግስት ለባለሀብቱ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባለፈ ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ ከክልሎች ጋር በጋራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ሰሞኑን በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የመከረ ፎረም በሀዋሳ ከተማ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም