ቀጥታ፡

በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች ፈቃድ ተሰጥቷል

ባህር ዳር፤ ህዳር 1/019 (ኢዜአ)፦ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የዞኑ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ገለፀ።

የመምሪያው የኢንቨስትመንት ዘርፍ ቡድን መሪ አቶ አበራ ገበየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ አልሚ ባለሃብቶችን ወደ አካባቢው በመሳብ የኢንቨስትመንት ዘርፉን የማሳደግ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ነው።

በበጀት ዓመቱ 120 ለሚሆኑ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት መታቀዱን ጠቅሰው፤ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 93 ለሚሆኑ ባለሃብቶች ፈቃድ መስጠት ተችሏል ብለዋል።

ባለሃብቶቹ 10 ነጥብ 34 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ሲሆን፣ ወደ ተሟላ ሥራ ሲገቡም ለ15 ሺህ 764 ወገኖች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በሩብ ዓመቱ ለ28 ባለሃብቶች ፈቃድ ለመስጠት የታቀደ ቢሆንም፣ በቅንጅት በተከናወነ ጠንካራ ሥራ ከዕቅድ በላይ ማከናወን እንደተቻለ ተናግረዋል።

ፈቃዱ የተሰጠውም በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በአገልግሎት እና መሰል የትኩረት ዘርፎች ላይ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች እንደሆነም አብራርተዋል።

በወተት ከብት እርባታ ፈቃድ ያገኙት አቶ ወርቁ አህመድ እንዳሉት፣ በዘርፉ ለመሰማራት የሚያስችላቸውን 7 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ተረክበው ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት ላይ ናቸው።

በዘርፉ በተሻለ እንቅስቃሴ ውጤታማ ለመሆን አቅደው እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸው፣ እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ቀልጣፋና የባለሃብቱን የመሥራት ፍላጎት የሚያነሳሳ መሆኑንም አስረድተዋል።

በዚህ ዓመት በእርሻና ሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ ወደ ሥራ ለመግባት ፈቃድ መውሰዳቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ሰውአገኝ ጥላሁን ናቸው።

የመምሪያው አሠራር ፍትሐዊና ቀልጣፋ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም በፍጥነት ወደ ልማት ለመግባት እያገዛቸው መሆኑን አንስተዋል።

በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከዚህ ቀደም በተለያየ ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ከ870 በላይ ባለሃብቶች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚሁ ውስጥ 559 የሚሆኑት ወደ ማምረት የገቡና አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም