ቀጥታ፡

የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር ለህብረ ብሄራዊ አንድነትና ለጋራ ትርክት ግንባታ መሰረት እየሆነ ነው

‎ሀዋሳ፣ህዳር 1/2019 (ኢዜአ)፡- የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር ለህብረ ብሄራዊ አንድነትና ለጋራ ትርክት ግንባታ መሰረት መሆኑን የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ እመቤት ኢሳያስ ገለጹ፡፡

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ እመቤት ኢሳያስ፤ ዘንድሮ ለ21ኛ  የሚከበረውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በተመለከተ እንደ ክልል የሚኖረውን አከባበር በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም የብሔር ብሔረሰቦች በዓል የኢትዮጵያ እምቅ ሃብትና ውበት በአደባባይ የሚታይበት፣ የሀገር መልካም ገጽታ የሚገነባበት የጋራ መድረክ መሆኑን አንስተዋል።

የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር ለህብረ ብሄራዊ አንድነትና ለጋራ ትርክት ግንባታ መሰረት መሆኑን በመግለጽ በክልል ደረጃ ይህንን በሚያሳይ መልኩ ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል የብዝሃነት መገለጫና የአብሮነት ማሳያ መሆኑን አንስተው በዓሉ አብሮነትን በሚያጠናክር፣ የጋራ ትርክትን በሚገነባና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በሚያጸና መልኩ ይከበራል ብለዋል።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከወዲሁ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮች የሚከናወኑ መሆኑን ያነሱት ምክትል አፈ ጉባኤዋ ህዳር 21 ክልላዊ የማጠቃለያ የአከባበር ሥነ-ሥርዐት የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል። 

የዘንድሮው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን “በብዝኃነት የደመቀች፣ በምክክር የፀናች ስልጡን ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ  በሀገር አቀፍ ደረጃ በጅማ ከተማ የሚከበር መሆኑ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም