ቀጥታ፡

የጋራ ድምፃችንን በማጠናከር፣ የአፍሪካ ከተሞችን የልማት ፍላጎት፣ የፋይናንስ ተደራሽነትና የቴክኖሎጂ ትብብር እናሳድጋለን - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 1/2019 (ኢዜአ) ፦ የጋራ ድምፃችንን በማጠናከር፣ የአፍሪካ ከተሞችን የልማት ፍላጎት፣ የፋይናንስ ተደራሽነትና የቴክኖሎጂ ትብብር እናሳድጋለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ ይገኛል።


 

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው በCOP31 በአንታሊያ ከአፍሪካ ልማት ባንክ የአየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አንቶኒ ኦኮን ንዮንግ እና የGlobal Covenant of Mayors አምባሳደር እና የፓሪስ ቀድሞ ከንቲባ አን ሂዳልጎ ጋር ተገናኝተን በአዲስ አበባ የአየር ንብረትና ዘላቂ የከተማ ልማት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተናል ሲሉ አስፍረዋል።


 

በተለይም የአየር ንብረት ፋይናንስን በቀጥታ ለከተሞች ማድረስ፣ የፕሮጀክት ዝግጅትና አፈጻጸም አቅምን ማጠናከር፣ እንዲሁም በአረንጓዴ ልማት፣ በወንዝ ዳርቻ ልማት፣ በከተማ መልሶ ማልማትና በከተማ ግብርና የተገኙ ልምዶችን ለመማማርና ለመለዋወጥ የሚያስችሉ የትብብር መስኮችን ለማጠናከር ተስማምተናል ብለዋል።


 

አዲስ አበባ የCOP32 አስተናጋጅ ከተማ በመሆኗ፣ የአፍሪካ ከተሞችን የጋራ የአየር ንብረት ቅድሚያዎች፣ የፋይናንስ ፍላጎቶችና የልማት አጀንዳ በአንድ ድምፅ ለዓለም ማቅረብ የሚያስችል መድረክ ለመፍጠር ትልቅ እድል አላት ሲሉም ገልጸዋል።

ከንቲባዋ አያይዘውም የጋራ ድምፃችንን በማጠናከር፣ የአፍሪካ ከተሞችን የልማት ፍላጎት፣ የፋይናንስ ተደራሽነትና የቴክኖሎጂ ትብብር እናሳድጋለን ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም