ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በገነባችው የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ተቋማዊ ስርዓት ለአፍሪካ ሀገራት ልምድ እያካፈለች ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 1/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ በገነባችው የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ተቋማዊ ስርዓት ለአፍሪካ ሀገራት ልምድ እያካፈለች እንደምትገኝ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሰረት መስቀሌ ገለጹ። 

የትልቅ ሀገር የትልቅ ሕዝብና የታላቅ ርዕይ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካርታ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች።

በዚህም በመደመር እሳቤ እየተመራች የአገልግሎት አሰጣጡን ከማዘመን ጀምሮ በርካታ ስራዎችን በማከናወን ከራሷ አልፋ ለቀጣናው የሚተርፉ እመርታዊ ውጤቶችን አስመዝግባለች።

ኢትዮጵያ የመንግሥት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓትን ( e-GP) የመንግሥት ግዥዎችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ወረቀት አልባ የአሰራር ስርዓት ዘርግታለች።

የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሰረት መስቀሌ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ባለስልጣኑ የሪፎርም ስራዎችን እየተገበረ ይገኛል።

የመደመር እሳቤ የተናጠል እሳቤዎችንና ጥረቶችን ወደ አንድ የጋራ ርዕይ፣ የቴክኖሎጂ አቅሞችንም ወደ ተጨባጭ ሀገራዊ ውጤት መቀየር መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) ስርዓት ስኬት የቴክኖሎጂ ለውጥ ብቻ ሳይሆን በጋራ ዓላማ፣ በትብብርና በተቋማት ቅንጅት የተገኘ እንደሆነ ተናግረዋል።

የመደመር መንግሥት የግዥና ንብረት አስተዳደር ስርዓቱን ማዘመን ያስቻለ ሪፎርም ማድረጉን ገልጸዋል።

ይህም በተቋሙ አሰራር ላይ ፈጣን ለውጥ ማምጣቱንና ባለስልጣኑ በ2023 ዓ.ም በዘርፉ በአፍሪካ ቀዳሚ የልምድና የእውቀት ማዕከል መሆን የሚያስችሉትን ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ለጋራ ዓላማ መደመር የጋራ አቅማችንን ለማጎልበትና የዕድገት ጉዟችንን ለማፋጠን ትልቅ አቅም እናገኛለን ያሉት ወይዘሮ መሰረት በዚህም ለአፍሪካ አርአያ የሚሆን ውጤት እያስመዘገብን ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሁሉም አውድ ዘመናዊ የህግ ማዕቀፍና የዲጂታል ስርዓት እየገነባች መሆኑን ጠቁመው፤ በመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ዘርፍም ለሞዛምቢክ፣ ሩዋንዳ፣ ናይጀሪያና ጋምቢያ እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ልምድ እያካፈለች ትገኛለች ብለዋል፡፡

በመደመር እሳቤ ብቃት ያለው አመራርና ባለሙያ መፍጠር እንዲሁም ዘላቂ የተቋማት ግንባታን ታሳቢ ያደረገ የሪፎርም ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም