ቀጥታ፡

የብልፅግና ፓርቲ የመደመር ፍልስፍና ለአፍሪካውያን አርዓያ የሚሆን አካታች የፖለቲካል ኢኮኖሚ ውጤት አስመዝግቧል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 1/2019 (ኢዜአ)፦ የብልፅግና ፓርቲ የመደመር ፍልስፍና ለአፍሪካውያን አርዓያ የሚሆን አካታች የፖለቲካል ኢኮኖሚ ውጤት ማስመዝገቡን የአፍሪካ ሀገራት ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

2ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ ከጥቅምት 26/2019 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 28/2019 ዓ.ም "ዕድገትን መምራት፤ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል።

በመክፈቻው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ከ54 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 1 ሺህ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ባለድርሻ አካላትና ተጋባዥ እንግዶች በተሳተፉበት በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዶ በስኬት ተጠናቋል።

የጉባዔው ተሳታፊ የአፍሪካ ሀገራት የፓርቲ ተወካዮች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ አካታች የፖለቲካል ኢኮኖሚ ምኅዳር በመፍጠር የሚደነቅ ተግባራዊ እርምጃ ወስዳለች።

በተለይም ዕድገትን በሚያፋጥን የብዝኅ ዘርፍ የልማት አቅጣጫና በሴቶች የአመራርና ውሳኔ ሰጪነት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ተምሳሌት የሚሆን አስደማሚ እርምጃ እየወሰደች መሆኗን ገልጸዋል።

የዚምባብዌ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ንቅናቄ ፕሬዝዳንት ሴናተር ዳግላስ ቶጋራ ምዎንዞራ፤ በአዲስ አበባ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ዘመናዊና ጽዱ የከተሜነት ምኅዳርን መፍጠር ያስቻሉ ናቸው ብለዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ጸጋዋን በመጠቀም የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ዕድገትን በሚያፋጥን ትክክለኛ የልማት አቅጣጫ ላይ መሆኗን እንደሚያመላክት ተናግረዋል።

በብዙ ሀገራት የተፈጥሮ ሀብት ትርፍ ለሌለው ግጭትና የጥቂቶች መጠቀሚያ ይውላል ያሉት ሴናተሩ፤ የኢትዮጵያ የልማት አካሄድ ግን ለአፍሪካውያን በተሞክሮነት የሚቀሰም ተምሳሌት ተግባር ነው ብለዋል።

በዚህም የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሕዝብ የገቡትን ቃል በመፈጸም፣ ዕዳን ወደ ምንዳ በመቀየርና ለዜጎች ተጠቃሚነት በማዋል የተሰናሰለ አህጉራዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አንስተዋል።

የኢትዮጵያን የልማት ተሞክሮም በዚምባቡዌ ለመተግበር እንፈልጋልን ብለዋል።


 

የሌሶቶ ካንያ ፓርቲ ተወካይ ኢሬን ምፋሃማ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ሴቶችን ወደ አመራርና ውሳኔ ሰጪነት በማምጣት አካታችና አሳታፊ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ምኅዳር እየገነባች ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አስደናቂ የዘመናዊ ከተማ ልማት እመርታዊ ልምድና ተሞክሮም በሀገራቸው መተግበር የሚያስችል ትምህርት ያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል።

በጉባዔው ላይ የነበራቸው የኢትዮጵያ ቆይታም የመደመር ፍልስፍና ሀገር በቀል እሳቤ በወረቀት ላይ የሰፈረ ብቻ ሳይሆን በተግባር የተገለጠ ውጤት ማምጣቱን እንደተገነዘቡ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ የኮሪደር፣ የወንዝ ዳርቻና ሌሎች የተሰናሰሉ የልማት ፕሮጀክቶችም ለአፍሪካውያን የቁርጠኝነትና የጠንካራ ሥራ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን አንስተዋል።

ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔም ከአፍሪካ ሕብረት «አጀንዳ 2063» ጋር የተጣጣሙና እስከ እ.ኤ.አ. 2040 የሚተገበሩ ኢኒሼቲቮችና የልማት አቅጣጫ ስምምነት አጀንዳዎች ተቀምጠውበታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም