ቀጥታ፡

የባሕር በር ባለቤትነትን ማረጋገጥ የመደመር ታላቁ ስትራቴጂ አንዱ እና ዋነኛው አካል ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 1/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ማፋጠን፣ የውጭ ንግድ ፍሰትን ማሳደግ እና የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስችል ዘንድ የባሕር በር ባለቤትነትን ማረጋገጥ የመደመር ታላቁ ስትራቴጂ አንዱ እና ዋነኛው አካል መሆኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ የማልማት የዘመናት ቁጭት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እውን በማድረግ ታሪክ ጽፋለች።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ የባሕር በር ባለቤትነት ታሪካዊ ጥያቄዋን ምላሽ ለማግኘትና ለማረጋገጥ እየሰራች እንደምትገኝ ተናግረዋል።

ይህ ጉዳይ ለዘመናት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሲነሳ የኖረ ምላሽ ያላገኘና በሀገራዊ ቁጭትነት የቆየ ታሪካዊ ጥያቄ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር መውጫዋን ማጣቷ በሀገራችን የታሪክ፣ የፖለቲካና የብሔራዊ ጥቅም ጉዞ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳረፈ ክስተት መሆኑን አንስተዋል።

በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ አመራር የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም እና የህዝቡን ጥያቄዎች አሳልፎ ለታሪካዊ ጠላቶች መስጠቱ በታሪክ ትልቁ ጠባሳ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በመንግሥት ላቅ ያለ የዲፕሎማሲ አካሄድ ኢትዮጵያ የባሕር በር ይገባታል የሚለው እሳቤ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጉዳይ እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ እንዳትገነባ በታሪካዊ ጠላቶቻችን የተፈጸመው ደባ በአንድነታችን እንደመከትነው ሁሉ አሁንም በሴራ ያጣነውን የባሕር በር በአንድነታችን አረጋግጠን የኢትዮጵያን ሥልጣኔ በከፍታ ላይ እንገነባለን ብለዋል።

ኢትዮጵያ አሁን የምትከተለው ሥልጡን አካሄድ ከወቅታዊ ፍላጎት ባለፈ የመጪዎቹን ትውልዶች ዕድል የሚወስን ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ ነው።

የመደመር ታላቁ ስትራቴጂም በ2050 ብልፅግናዋን ያረጋገጠች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበረችና የተፈራች ሀገር መገንባትን ዓላማ ማድረጉን አብራርተዋል።

ይህ ስትራቴጂ የዛሬን ችግሮች ብቻ ለመፍታት ሳይሆን የነገውን ትውልድ የልማት፣ የኢኮኖሚና የሉዓላዊነት ፍላጎቶች ታሳቢ ማድረጉንም ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በራሷ ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶቿን በአግባቡ ማልማት፣ የዓባይን ወንዝ ጨምሮ ያሏትን ሀብቶች ለሕዝቦቿ ብልፅግና ማዋልና የሀገራችን የኢኮኖሚ አቅም ማሳደግ ዋነኛ የልማት አቅጣጫዎች አድርጋለች ብለዋል።

የባሕር በር ባለቤትነትን የማረጋገጥ ጉዳይም የዚሁ ስትራቴጂ አንዱ አካል መሆኑን አስረድተዋል።

ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላትና በሕዝብ ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገራት መካከል የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ የባሕር መውጫ አለመኖሩ በንግድ፣ በትራንስፖርትና በኢኮኖሚያዊ ትስስር ላይ የሚፈጥረው ጫና ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ስለሆነም የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄዋ በሕጋዊ፣ በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍትሔ ማግኘቱ ለሀገሪቱ የወደፊት እድገት ወሳኝ ነው ብለዋል።

ግብፅ እና ተላላኪዎቿ ኢትዮጵያ በድህነት ውስጥ እንድትቆይ ፍላጎታቸው መሆኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ የዓባይን ውሃ የማልማት ታሪካዊ ቁጭቷን በተግባር እንዳረጋገችው ሁሉ፣ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄዋንም በሀገራዊ አንድነት፣ በጠንካራ ዲፕሎማሲና በሕጋዊ አካሄድ ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም