የማይቆራረጠው የመረጃ መረብ - ኢዜአ አማርኛ
የማይቆራረጠው የመረጃ መረብ
የአፋር ምድር በእምቅ የተፈጥሮ ሃብት፣ በቅርስና ታሪክ፣ በቱሪዝም መስህብነት የሚጠቀስ አካባቢ መሆኑ ይታወቃል። የአፋሮች ውብ ባህሎችና የአኗኗር ዘይቤዎች፣ አልባሳት፣ የምግብና ሌሎችም ልዩ መገለጫዎችና የካበቱ እሴቶች የሚያስደንቁ ናቸው። የአዋሽ ወንዝ በክልሉ የመስኖ ልማት በረከት ሆኖም እያገለገለ ይገኛል። የአፋር ክልል ጥጥ የሚለማበት፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ለቴምር ምርት እምቅ አቅም ያለው መሆኑም ይታወቃል።
በአፋሮች ዘንድ ከትውልድ ትውልድ የተላለፉ፣ የሕዝቡን ጠንካራ አብሮነትና ማኅበራዊ ትስስር የሚገልጹ እሴቶችም ልዩ ስፍራ አላቸው። በአፋር ሕዝብ ዘንድ ልዩ ቦታ የሚሰጠው “ዳጉ” እየተባለ የሚጠራው የመረጃ ልውውጥ ከእነዚህ እሴቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። የማይቆራረጠውና እሴቱ ተጠብቆ ዘመናትን የዘለቀው የመረጃ መረብ “ዳጉ” የመረጃ ልውውጥ ብቻ ሳይሆን የማኅበራዊ ሕይወት ትስስር መሰረት፣ የእርስ በርስ ቁርኝት ሰንሰለት፣ የአብሮነት ካስማና የትብብር መገለጫቸው ጭምር ነው።
በዳጉ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት ውስጥ ሰዎች በመንገድ፣ በገበያ፣ በጉዞ ላይ ወይም በሌላ ማኅበራዊ ግንኙነት ሲገናኙ የሰሙትንና ያዩትን አስፈላጊ መረጃ የሚለዋወጡበት የመረጃ ሰንሰለታቸው ነው። የዳጉ ልዩነት ሰዎች የሚያውቋቸው ወዳጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን በመንገድ ላይ የሚያገኟቸውን እንግዶችም ጭምር የመረጃ ልውውጡ አካል ማድረጉ ነው። ሁለት ሰዎች በመንገድ ሲገናኙ እርስ በርሳቸው የሰሙትን፣ ያዩትንና ከሚመጡበት አካባቢ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በመጠያየቅ የመረጃ ልውውጥ ያደርጋሉ።
በአፋር ሕዝብ ዘንድ የዳጉ ውይይት የሚጀምርባቸው ጥያቄዎችም ልዩ ትርጉም አላቸው። ከእነዚህም መካከል "ጆሮህ ምን ሰማ?" እና "ዓይንህ ምን አየ?" የሚሉ ጥያቄዎች ይጠቀሳሉ። እነዚህ ጥያቄዎች የሚያመለክቱት መረጃው ከየት እንደመጣ፣ በማን እንደተሰማና በምን ዓይነት ማስረጃ ላይ እንደተመሠረተ ለማወቅ ሚያስችሉ ናቸው። በዚሁ መሰረትም ዳጉ በአፋሮች ዘንድ ከጥንት እስከ ዛሬ የመረጃ መለዋወጫና የማህበራዊ መገለጫ እሴት ሰንሰለት ሆኖ ቀጥሏል።
የዳጉ ዋና ዋና ይዘቶችና የመረጃ ሽፋን በአንድ የሕይወት ዘርፍ ብቻ የተገደበ አይደለም። ከግለሰብ ሕይወት እስከ ማኅበረሰብ አጠቃላይ ጉዳዮች ድረስ የሚዘልቅ ሰፊ የመረጃ ሽፋን አለው። በመረጃ ልውውጡ ከሰዎች አልፎ ከእንስሳት በተለይም ከግመሎቻቸው የውሃ እና የግጦሽ ሁኔታ ጋር የተገናኘ ሊሆን ይችላል። የደኅንነት መረጃን መሰረት በማድረግም ስለ ግጭት፣ ስለ አደጋ፣ ስለ የመንገድ ሁኔታና ስለ ሌሎች ሊያስጠነቅቁ የሚችሉ ክስተቶች መረጃ መለዋወጥ የግድ ይላቸዋል። በማህበረሰቡ ዘንድ አዳዲስ ክስተቶች ካሉ፤ የሰርግ እና የለቅሶ ጉዳይና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችም በዳጉ የመረጃ ስርአት የሚቃኙ ይሆናል።
በዳጉ የሚረሳ ጉዳይና የሚናቅ መረጃ ባለመኖሩ የእንስሳት የገበያ ዋጋ፣ የምርት ሁኔታ፣ የንግድና ሌሎችም ሁኔታዎች ሊቃኙ ይችላሉ። የአካባቢው የአየር ሁኔታ ተቃኝቶ ዝናብ ስለመኖሩ፣ የጎርፍና ሌሎች ተያያዥ ክስተቶችም ካሉ መረጃው ከአንዱ ጥቅ ወደ ሌላው ጥግ በዳጉ ይደርሳል።
የዳጉ ዋነኛ መርህ፡ እውነት፣ ታማኝነትና ኃላፊነት ሲሆን መረጃን ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን የመረጃውን ትክክለኛነትና ምንጩን ማረጋገጥ የግድ ነው። በዳጉ ሥርዓት ውስጥ አንድ ሰው የሰማውን መረጃ ከየት እንደሰማ፣ ከማን እንደተቀበለና ምንጩ ምን እንደሆነ በተሟላ መልኩ የማስተላለፍ ሃላፊነት አለበት። ሐሰተኛ ወይም ያልተረጋገጠ መረጃ ማስተላለፍ በአፋር ባህላዊ ሥርዓት እንደ ከባድ ጥፋት ይቆጠራል። የዳጉን ሥርዓት መጣስም ከባህላዊው የማኅበረሰብ ሕግ ከሆነው ማዳዓ (Mada'a) ጋር በተያያዘ የማኅበረሰቡን ተጠያቂነት ሊያስከትል ይችላል።
በዳጉ መርህ መሰረት እውነትን ማስቀደም፣ የመረጃ ምንጭን መግለጽ (መረጃው ከየትና ከማን እንደተገኘ) እንዲሁም ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን ሳይደብቁ ለሌሎች ማካፈል የግድ ይላል። በመሆኑም ዳጉ የመረጃ ልውውጥ ብቻ ሳይሆን የጠንካራ ማህበራዊ ግንኙነት መሰረት፣ የህዝቡ የሞራልና ስነ ምግባር እሴት መገለጫ ነው ማለት ይቻላል።
የዳጉ ሥርዓት ከመረጃ ልውውጥ ባሻገር ሰዎች የሚጠያየቁበት፣ በችግሮቻቸው ዙሪያ ተነጋግረው የሚረዳዱበትም ነው። ለምሳሌ አንድ አርብቶ አደር በሌላ አካባቢ የውሃ ምንጭ መኖሩን ወይም የግጦሽ መሬት መገኘቱን ካወቀ፣ ይህንን መረጃ ለሚያገኘው ሌላ ሰው ያስተላልፋል። ይህም የእንስሳትን ጤና፣ የቤተሰቦችን ኑሮና የማኅበረሰቡን የምግብ ዋስትና ለመጠበቅ ይረዳል።
ዳጉ ከሌሎች ባህላዊ የአፋር ማኅበራዊ ተቋማትም ጋር ተያይዞ ይሠራል። ለምሳሌ ዳጉ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚገኝን መረጃ የማሰባሰብና የማስተላለፍ ሚና ሲኖረው፣ አዳ (Adda) የባህላዊ አስተዳደርና ውሳኔ ሰጪነት ሚና ይወጣል። በተጨማሪም ኤዶ (Edo) የግጦሽና የተፈጥሮ ሀብት ሁኔታን ቀድሞ የሚመረምር ባህላዊ ሥርዓት ነው። እነዚህ ሥርዓቶች ተደጋግፈው ለአርብቶ አደሩ የኑሮ ውሳኔዎች ድጋፍ ይሰጣሉ። ዳጉ በዋናነት የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት ሲሆን ማዳዓ ደግሞ የአፋር ባህላዊ ሕግና ሥርዓት ነው። የግጭት አፈታት የማኅበረሰብ ሥርዓትና የተጠያቂነት ጉዳዮች ከማዳዓ ጋር ይያያዛሉ። ዳጉ የሚያቀርበው መረጃም በእንዲህ ያሉ ማኅበራዊ ውሳኔዎች ላይ ጠቃሚ መሠረት ሊሆን ይችላል።
በዳጉ የቀድሞ የመረጃ ልወውጥ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ በሰው ለሰው ግንኙነት፣ በጉዞና በቀጥታ ውይይት ይተላለፍ የነበር መሆኑ ይታወቃል። አሁን ላይ ግን የሞባይል ስልክና የዘመናዊ መገናኛ ቴክኖሎጂዎች መስፋፋት የዳጉን የመረጃ ልውውጥ አቅም አስፍተውታል። ሰዎች በአካል ሳይገናኙ ስለ የተለያዩ አካባቢዎች ሁኔታ በስልክ መረጃ መለዋወጥ ይችላሉ። በዘመናዊው የመረጃ መለዋወጫ መንገድ ቢታገዝም የዳጉ መሠረታዊ ባህላዊ መርሆች ግን የተከበሩና የተጠበቁ ናቸው። የመረጃ ምንጭን ማረጋገጥ፣ እውነትን ማስቀደምና ለማኅበረሰቡ ኃላፊነት መውሰድ የዳጉ መሠረታዊ እሴቶች ሆነው ቀጥለዋል።
በመሆኑም ዳጉ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ የተላለፈ የአፋር ሕዝብ የእውቀት ሀብት ነው። በዚህ ሥርዓት ውስጥ ወጣቶች ከአዛውንቶች ብዙ ይማራሉ፤ ልምድን፣ የአካባቢ እውቀትንና ማኅበራዊ ኃላፊነትን ይቀስማሉ። የአፋር አዛውንቶች በሕይወት ያካበቱትን ልምድ ለወጣቶች በማካፈል የዳጉን ሥርዓት እንዲጠብቅና እንዲያስቀጥል ያግዛሉ።
የአፋር ሕዝብ ዳጉ በዓለም ላይ ካሉ ልዩ ባህላዊ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓቶች መካከል የሚጠቀስ የማንነት መገለጫ ነው። ዘመናዊው ዓለም በኢንተርኔትና በዲጂታል ቴክኖሎጂ መረጃን በሰከንዶች ማስተላለፍ በቻለበት ዘመን፤ ዳጉ ከዘመናት በፊት በሰው ለሰው ግንኙነት የተገነባ የመረጃ መረብ መሆኑ የሚያስደንቅ ነው። በመሆኑም ይህንን እምቅ ሃብት ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍና የሀገር ሃብት አድርጎ መጠቀም ያስፈልጋል።