ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ጥራቱ የተረጋገጠ የቡና ምርትን ለገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው

ባህር ዳር፤ ህዳር 1/2019 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ጥራትና ደህንነቱ የተረጋገጠ የቡና ምርት ሰብስቦ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ውስጥ የቡና ዘርፍ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት እና የብዙ ሚሊዮን ዜጎችን ኑሮ በመደገፍ ረገድ ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል። 

በአማራ ክልል በዋናነት በምዕራብ ጎጃም፣ በደቡብ ጎንደር፣ በምስራቅ ጎጃም እንዲሁም በአዊ ዞን አግሮ-ኢኮሎጂያቸው ለቡና ልማት ተስማሚ የሆኑ ሰፋፊ መሬቶች ይገኛሉ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ የቡና ምርት ጥራት እና ደህንነት ላይ አተኩሮ መስራቱ የገበያ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ፣  ለህገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር፣ ለአካባቢው አምራቾች ተጠቃሚነት እና ለሀገር ውስጥ አቅርቦት እና የጥራት ደረጃ መሻሻል  ጉልህ ፋይዳ  ይኖረዋል።


 

በመሆኑም ቢሮው ምርት ከመሰብሰብ ጀምሮ እስከ ማዘጋጀት፣ ማጓጓዝ እና ለገበያ ማቅረብ ባለው ሙሉ እሴት ሰንሰለት ላይ የቴክኒክ እና ቁጥጥር ድጋፍ ማድረጉ ለዘርፉ እድገት ቁልፍ ተግባር ነው።


 

የቢሮው የሆርቲካልቸር ልማትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ አበበ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ለቡና ልማት ተስማሚ በሆኑ አካባቢዎች 36 ሺህ 135 ሄክታር መሬት በቡና ተክል እየለማ ነው።

በቡና ልማቱም ከ572 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳፉ እንደሚገኝ ጠቅሰው የምርት ጥራትን ለማስጠበቅ የባለሙያ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።  

እየለማ ከሚገኘው መሬት ውስጥ ለምርት ከደረሰው 22 ሺህ ሄክታር መሬት በምርት ዘመኑ 141 ሺህ ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል። 

በአሁኑ ወቅት እየተሰበሰበ ያለውን የቡና ምርት የጥራት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አድርቆና ፈልፍሎ ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።

ከሚሰበሰበው ውስጥም 6 ሺህ 800 ኩንታል ምርት ለውጭ ገበያ የሚቀርብ መሆኑን ገልጸው፤ አርሶ አደሩ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአማራ ክልል የሚመረተው ቡና መለያ ስም እንዲያገኝና በዓለም ገበያ ታዋቂ እንዲሆን ቢሮው ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር  በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ልማቱን በቀጣይ ይበልጥ በማስፋፋትና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሁሉን አቀፍ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

በአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የወራሚት የአትክልትና ፍራፍሬ ምርምርና ስልጠና ንዑስ ማዕከል የቡና ተመራማሪ አቶ መለሰ ዋለ እንደገለፁት፤ ማዕከሉ ለደጋና ለወይና ደጋ የሚሆኑ የተለያዩ የቡና ዝርያዎችን ሲያሰራጭ ቆይቷል።


 

ከጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል የወጡና በሰርቶ ማሳያ ቦታዎች በሄክታር እስከ 18 ኩንታል ምርት የሚሰጡ ሶስት የቡና ዝርያዎችን ወደ አርሶ አደሩ እንዲደርሱ ማድረግ እንደተቻለም ገልጸዋል።

‎የክልሉ መንግስትም ለቡና ልማት ትኩረት በመስጠቱ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ሶስት የቡና ዝርያዎችን በማላመድና በቲሹ ካልቸር በማባዛት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ማዕከሉ ምክረ ሃሳብ ማቅረቡን አመልክተዋል።

በክልሉ ባለፈው ዓመት 130 ሺህ ኩንታል የቡና ምርት ተሰብስቦ ለአካባቢ ገበያ መቅረቡን የቢሮው መረጃ ያመለክታል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም