ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ትብብር ላይ የተሸረሸረውን እምነት መልሶ መገንባት ቀዳሚ ትኩረቷ ነው - ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ትብብር ላይ የተሸረሸረውን እምነት መልሶ መገንባት ቀዳሚ ትኩረቷ ነው - ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ህዳር 1/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ትብብር ላይ የተሸረሸረውን እምነት ዳግም መልሶ መገንባትን ዋና ትኩረቷ አድርጋ እንደምትሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ፕሬዝዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
የአየር ንብረት ግቦችን ለማሳካት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አቅርቦቱ ፍትሃዊ መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል።
31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ ይገኛል።
“ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት ወደተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን” የጉባኤው መሪ ቃል ነው።
በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ ተሳትፎ እያደረገች ትገኛለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከጉባኤው ጎን ለጎን በተካሄደ ስብስባ ላይ ተሳትፈዋል።
ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በስብስባው ላይ ባደረጉት ንግግር በአየር ንብረት ቀውስ ለተጎዱ ሀገራት ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በአሁኑ ወቅት ከባድና ውሳኔ የሚሹ ታሪካዊ ፈተናዎች ከፊቱ ተደቅነውበታል ብለዋል።
የአየር ንብረት ቀውሱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣቱን ጠቅሰው ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች ዓለም አቀፍ ትብብርን እየፈተኑ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ግንኙነቶች ከብሔራዊ ደህንነት ፍላጎቶች አንጻር እየተቃኙ መሆናቸውንም ነው ያነሱት።
ሚኒስትሩ ሀገራት በቴክኖሎጂ፣ በኢንቨስትመንት እና በንግድ በሚያደርጓቸው ፉክክሮች የተነሳ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ የመከላከል ጥረቶች እየተሸረሸሩ መምጣታቸውን አብራርተዋል።
ሀገራት የሚፈለገውን የአየር ንብረት ፋይናንስ ሳያገኙ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን እንዲቀንሱ እና ጫናዎችን እንዲቋቋሙ ከፍተኛ ኃላፊነት እየተጣለባቸው እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ሳይንሳዊ ሪፖርቶችን በዋቢነት ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የሙቀት መጨመርን መቆጣጠር፣ ተጽእኖዎችን የመቋቋም ዝግጁነት ክፍተቶችን መሙላት እና ለጉዳትና ኪሳራዎች ፈጣን መፍትሄ መስጠት የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።
የፋይናንስ አቅርቦት ክፍተቱ ሳይሞላ የልቀት ቅነሳንና የዝግጁነት አቅምን ማጠናከር ሊታሰብ የማይችል ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የኮፕ 32 ጉባኤ በሊቀመንበርነት ለመምራት በምትዘጋጅበት በዚህ ወቅት፣ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ትብብር ላይ የተሸረሸረውን እምነት መልሶ መገንባት ላይ ዋና ትኩረቷ አድርጋ እንደምትሰራ ተናግረዋል።
እምነቱን መልሶ ለማግኘት በተግባር የተደገፈ አፈጻጸም፣ አካታች አሰራር፣ ልዩነቶችን በውይይት መፍታትና ዓለም አቀፍ ግቦችን ከሀገር ውስጥ እቅዶች ጋር ማቀናጀት እንደሚገባ አመልክተዋል።
የአየር ንብረት ትብብርን ለዓለም አቀፍ አንድነት ዋነኛ መደላድል ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።