ቀጥታ፡

በምስራቅ ኦሮሚያ ዞን የጽዱ ጤና ተቋማት ትግበራ የተሻለ የህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ አስችሏል

ጭሮ ፣ህዳር 1/2019 (ኢዜአ)፡-የጽዱ ጤና ተቋማት ትግበራ ተቋማቱን ማራኪ ከማድረጉም በላይ የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት ጥራት በማሻሻል በኩል ትልቅ ለውጥ ማምጣቱን በምስራቅ ኦሮሚያ ዞን የሸነን ዱጎ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

በኢትዮጵያ በጤናው ሴክተር በስፋት እየተተገበረ የሚገኘው "ጽዱ ጤና ተቋም" ንቅናቄ ዋና አላማ፣ የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ጥራት ማሻሻል፣ የኢንፌክሽን ስርጭትን መግታት እና የታካሚዎችን ደህንነት ማረጋገጥ ነው።

የጤና ሚኒስቴር እና የክልል ጤና ቢሮዎች የጤና ተቋማትን አካባቢ ማራኪ፣ ጽዱ እና አስተማማኝ የማድረግ መርሃ-ግብር ዘርግተው ወደ ትግበራ ገብተዋል። 

በምስራቅ ኦሮሚያ ዞን ሸነን ዱጎ ወረዳ የተመዘገበው ውጤትም የዚህ ሀገር አቀፍ ጥረት አካል ሲሆን፣ የህብረተሰቡን እርካታ ከመጨመሩም በላይ የታካሚዎችን የህክምና አገልግሎት የማግኘት እድል እንዲያድግ ማስቻሉ ይገልጻል።


 

በዞኑ የሸነን ዱጎ ወረዳ መሰላ ከተማ ነዋሪ  ወይዘሮ ወርቄ ደምሴ በሰጡት አስተያየት የጽዱ ጤና ተቋማት ንቅናቄ የአከባቢውን ህብረተሰብ እያሳተፈና ተጠቃሚም እያደረገ ይገኛል።

ከዚህ ቀደም በየጤና ተቋማቱ  የንፅህና ጉድለትና  የማረፊያ ቦታ እጥረት ይታይ እንደነበር ጠቅሰው፤  አሁን  ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል።

በተለይም በወረዳው ጤና ተቋማት የህፃናት ማቆያና የታካሚዎች ማረፊያ መዘጋጀቱ ካለምንም እንግልት የተሻለ የህክምና አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል ብለዋል።

ንቅናቄው ከተቋማት ንፅህናን ከመጠበቅ ባለፈ ህብረተሰቡ በጋራ በመሆን  አካባቢውን በማፅዳት  ከተላላፊ በሽታዎች እራሱን እንዲጠብቅ አስችሏል ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ፍሬ አስራት ናቸው።


 

በወረዳው በቂ የህክምና ባለሙያዎች በመመደባቸውም ከዚህ ቀደም  ከፍተኛ ህክምና ፍለጋ  ወደ ሂርና ከተማ  ሲያደርጉት የነበረው  ጉዞና እንግልት ማስቀረቱን አስረድተዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አብደላ ከሊል እንዳሉት በጤና ተቋማት የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ቅልጥፍና በመሻሻሉ  እሳቸውን ጨምሮ  የተጠቃሚዎችን እርካታ አሳድጓል።

ከቀዶ ጥገና እስከ ከፍተኛ ህክምና በቂ ሀኪሞች ተሟልተው በወረዳ ጤና ጣቢያ ደረጃ አገልግሎት እያገኙ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

በጤና አገልግሎቱ ዙሪያ እየተተገበረ ያለው የለውጥ ስራ በመድሃኒት አቅርቦት ረገድ የነበረውን ችግር  በተሟላ መልኩ ማቃለሉንም አክለዋል።

የሸነን ዱጎ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሙራድ አህመድ የጤና አገልግሎት አሰጣጡን የተሟላ፣ ተደራሽና ተገልጋዩን የሚያረካ ለማድረግ የጽዱ ጤና ተቋማት  ንቅናቄ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ  ገልጸዋል።

ንቅናቄው የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድን ዘመናዊ ማድረግ፣ የጤና ተቋማት ምድረ ግቢ በማስዋብ ለተገልጋይ ምቹ ማድረግን ያካትታል ብለዋል።


 

እንዲሁም ከወረቀት ነጻ የሆነ የዲጅታል አሰራር መዘርጋትና የአገልግሎት አሰጣጥን ቀጣይነት ባለው መልኩ ማሻሻል ላይ ትኩረት ማድረጉን አስረድተዋል።

በዚህ ረገድ በወረዳው ከሚገኙ ሰባት ጤና ጣቢያዎች ውስጥ በአምስቱ የዲጂታል አሰራር ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረጉን አብራርተዋል።

ይህም የአገልግሎት ጥራትን ከማሻሻል ባለፈ የአሰራር ቅልጥፍናን ለማሳደግ አግዟል ብለዋል።

ህብረተሰቡ የመኖሪያ አካባቢውን በጋራ እንዲያፀዳና ንፅህናውን እንዲጠብቅ የማስተማርና የማነቃቃት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፣ የመድሃኒት አቅርቦትን ዘመናዊና በጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እንዲመራ ለማድረግ አዳዲስ አሰራሮች መዘርጋታቸውን አቶ ሙራድ አስረድተዋል።

የመሰላ ጤና ጣቢያ ሀኪም ዶክተር በያንሳ ሂርጳ በበኩላቸው፣ንቅናቄው የጤና ተቋማትን ከህክምና አገልግሎት መስጫነት ባለፈ ለታካሚዎች ምቹና  አስደሳች  የቆይታ አካባቢ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የጤና ተቋማት ንፁህና ማራኪ መሆናቸው ለታካሚዎች የአእምሮ እርካታ ከመስጠቱም በላይ ለጤና አጠባበቅ ወሳኝ ሚና እንዳለው  አመልክተዋል።

ዶክተር በያንሳ እንዳሉት፣ የመሰላ ጤና ጣቢያ በምስራቅ ኦሮሚያ ዞን የቀዶ ጥገና አገልግሎት የጀመረ የመጀመሪያው ጤና ጣቢያ ሲሆን፣ የተሟላ የህክምናና የምርመራ መሳሪያዎችም ተሟልተውለታል። 

ይህም በንቅናቄው እየተመዘገበ ካለው ውጤት አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም