ቀጥታ፡

አረንጓዴው የፋይናንስ ድልድይ

የካርቦን ንግድ ማለት የካርቦን ዳይኦክሳይድ እና ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥን የሚያስከትሉ ጋዞችን ልቀትን ለመቆጣጠር የሚደረግ ዘመናዊ የገበያ ዘዴ ነው።

ልክ እንደ ሌሎች ምርቶች ሁሉ የካርቦን ልቀትን የመገበያያ ዕቃ አድርጎ የሚቆጥረው ይህ ስርዓት፣ መንግስታት ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኩባንያዎች ወይም ተቋማት ሊለቁት የሚችሉትን ከፍተኛውን የካርቦን መጠን “የልቀት ጣሪያ” በማለት እንዲወስኑ ያደርጋል።

ከዚያም እያንዳንዱ ኩባንያ የታዳሽ ኃይል ወይም የደን ልማትን በመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ የካርቦን ጋዝ ልቀትን ሲቀንስ ብድር ወይም የካርቦን ክሬዲት የሚያገኝበት አሰራር ይተገበራል። ይህ የካርቦን ንግድ ሀገራት፣ ኩባንያዎች እና ግለሰቦች በተገዢነት እና በፈቃደኝነት ላይ ተመስርተው የሚያከናውኑት ዓለም አቀፋዊ የፋይናንስ ፍሰት መስመር ነው።

አፍሪካ በዓለም ደረጃ ወደ ከባቢ አየር በሚለቀቀው በካይ ጋዝ ልቀት ከአራት በመቶ ያነሰ ድርሻ ቢኖራትም የአየር ንብረት ለውጥን ከፍተኛ ዳፋ እና ጉዳት በግንባር ቀደምትነት የምትሸከም አህጉር ሆናለች።

ይህንን ተፅዕኖ ለመቋቋም እና ፍትሃዊ የአየር ንብረት ፋይናንስን ለማግኘት የአፍሪካ ሀገራት በግብጽ ሻርም አል ሼክ በተካሄደው 27ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንበረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የአፍሪካ ካርቦን ገበያ ኢኒሼቲቭን ይፋ አድርገዋል። በኢኒሼቲቩ አማካኝነት አህጉሪቱ በየዓመቱ በ300 ሚሊዮን የካርቦን ክሬዲት ስድስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ያቀደች ሲሆን፣ እ.አ.አ በ2030 በካርቦን ንግድ አማካኝነት ለ30 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ሰፊ ውጥን ይዛ በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች።


 

የካርቦን ገበያ በአፍሪካ ሀገራት ተስፋ ሰጪ እድገት እያሳየ የሚገኝ ሲሆን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ፣ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ እና ሴኔጋል የካርቦን ገበያ የአሰራር ማዕቀፎችና ግቦች አዘጋጅተው ወደ ተግባር ገብተዋል። የአፍሪካ ልማት ባንክ የካርቦን ገበያ የፋይናንስ አማራጭ በማዘጋጀት ሀገራት ማዕቀፎች እንዲቀርጹና የካርቦን ክሬዲት በአፍሪካ የአክሲዮን ገበያዎች ውስጥ እንዲካተት ያደረገ ሲሆን፣ የአፍሪካ ሕብረት የልማት ኤጀንሲ (አውዳ-ኔፓድ) ደግሞ የግብይት ስርዓቱን የሚወስን ማዕቀፍ አዘጋጅቶ በመተግበር ላይ ይገኛል።

ይህ ማዕቀፍ የካርቦን ገበያ ማህበረሰቦች ካርቦንን በማመቅ ስራቸው ተጨባጭ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥና ለብዝበዛ እንዳይጋለጡ ክትትልና ድጋፍ የሚደረግበት ዋነኛ መንገድ ሆኖ ያገለግላል።

ዛሬ በቱርኪዬ አንታሊያ ከተማ በይፋ የተጀመረው 31ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP31) ለአለም አቀፉ የካርቦን ገበያ ትልቅ ታሪካዊ ምዕራፍ ይዞ መጥቷል።

በጉባኤው ላይ የፓሪስ ስምምነት አንቀጽ 6ን መሰረት ያደረገው የዓለም አቀፍ ካርቦን ገበያ ደንቦችን ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባራዊ ሽያጭ ማሸጋገር ከጉባኤው አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳል።

ይህ መድረክ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት እና የካርቦን ገበያ የአሰራር ማዕቀፍ በመዘርጋት ረገድ እያከናወነች ያለችውንና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆነውን ተግባር ለዓለም የምታሳይበት ሆኗል።

የኮፕ 31 የድርድር ሂደት በቀጥታ ከኢትዮጵያ ቀጣይ ታሪካዊ ኃላፊነት ጋር የተቆራኘ ነው፤ ሀገሪቷ እ.አ.አ በ2027 የሚካሄደውን 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) በአዲስ አበባ ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ ትገኛለች።

በመሆኑም በአንታሊያ ዛሬ የተጀመሩት የካርቦን ገበያ ውይይቶች እና የሚወሰኑት ውሳኔዎች በቀጥታ ወደ አዲስ አበባው የኮፕ 32 የትግበራ መድረክ የሚሸጋገሩ በመሆናቸው ለሀገራችን ስትራቴጂካዊ ፋይዳቸው እጅግ የላቀ ነው።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር በቢሾፍቱ ከተማ በ2017 ዓ.ም ባካሄደው የውይይት መድረክ የብሔራዊ የካርቦን ገበያ ስትራቴጂ የመጨረሻ ረቂቅ እና የህግ ክፍተት ዳሰሳ ጥናት ሪፖርትን መገምገሙን ተከትሎ፣ ሀገሪቱ አሁን ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀውን የብሔራዊ የካርቦን ገበያ አዋጅ ቁጥር 1436/2026 በይፋ ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች።

ይህ አዋጅ እና የተቀረጸው አዲሱ ብሔራዊ የካርቦን ገበያ ስትራቴጂ (2025–2035) ኢትዮጵያ በደን ልማት፣ በትራንስፖርት፣ በቆሻሻ አወጋገድ እና በታዳሽ ኃይል አማራጮች ላይ በምታበረክተው ልክ ተጠቃሚ የሚያደርጋት ህጋዊና ተቋማዊ መሰረት ጥሏል።

በዚህም ሙቀት አማቂ ጋዞችን በመቀነስ፣ አረንጓዴ ኢኮኖሚ በማሳለጥና የዜጎችን ተጠቃሚነት በማሳደግ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራን ለማገዝ ጉልህ ፋይዳ ያለው መሆኑ ተረጋግጧል።

ኢትዮጵያ ከኖርዌይ መንግስት ጋር የተፈራረመችው እና እ.አ.አ እስከ 2026 ድረስ የሚቆየው የ75 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የካርቦን ሽያጭ ስምምነት ሀገሪቱ በካርቦን ግብይቱ እያገኘች ያለችውን ተጨባጭ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በግልጽ ያሳያል።

ከዚህ የካርበን ሽያጭ የተገኘው ገቢ እንደ ሀገር የተሰሩ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስራዎችን ለማጠናከር እንዲሁም አዳዲስ የደን ልማት ስራዎችን ለመስራት እየዋለ ይገኛል። በተለይም በባሌ እና በምዕራብ አርሲ ጥብቅ ደኖች ሲተገበር በቆየው የበካይ ጋዞች ቅነሳና የደን ጭፍጨፋን የመቀነስ ፕሮጀክት (ሬድ ፕላስ) አማካኝነት እየተከናወነ ያለው የካርቦን ንግድ ጉዳት ይደርስበት የነበረውን የደን ሀብት ከመጠበቁ ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ገቢ እያስገኘ ይገኛል።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2030 የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን በ68.4 በመቶ ለመቀነስ ያስቀመጠችውን ታላቅ ሀገራዊ ግብ ለማሳካት በአጠቃላይ 316 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋታል።

ዛሬ በቱርኪዬ የተጀመረው እና በሚቀጥለው ዓመት በአዲስ አበባ በሚካሄደው ኮፕ 32 ላይ ትልቅ የትግበራ ምዕራፍ የሚይዘው የካርቦን ገበያ ንግድ፣ ይህንን ግዙፍ የፋይናንስ ፍላጎት በፍትሃዊ መንገድ ለመሙላት እና የሀብት ማፈላለግ ስራዎችን ለማገዝ የላቀ ሚና ይጫወታል።

ሀገሪቱ አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ በተለያዩ ጥብቅ ደኖች ውስጥ ካርቦኖችን በማከማቸት ገቢ ለማግኘት የምታደርገው ጥረት፣ የካርቦን ግብይት የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ የማግኘት አማራጭን በማስፋት ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ለመሆኑ ህያው ምስክር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም