ኮፕ 32 ከንግግሮች ባለፈ ዘላቂ መፍትሄ የሚመጣበት ጉባኤ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን- የኮፕ 31 ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኮፕ 32 ከንግግሮች ባለፈ ዘላቂ መፍትሄ የሚመጣበት ጉባኤ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን- የኮፕ 31 ተሳታፊዎች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2019 (ኢዜአ)፦ 32ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) ኮፕ 32 ከንግግሮች ባለፈ ዘላቂ መፍትሄ የሚመጣበት እና ተጨባጭ እርምጃዎች የሚወሰዱበት ጉባኤ ይሆናል ብለው እንደሚጠብቁ የኮፕ 31 ተሳታፊዎች ገለጹ።
ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱ ለአፍሪካ ትልቅ ድል መሆኑንም ተናግረዋል።
31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) በቱርኪዬ አንታሊያ ዛሬ ተጀምሯል።
“ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት ወደተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን” የጉባኤው መሪ ቃል ነው።
የሞዛምቢክ የግብርና፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የዓሣ ሀብት ሚኒስቴር ተወካይ ሉዊስ ንያሙሽ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ እና በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ እያሳየችው ያለው መሪነት ለአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው።
አዲስ አበባም ዘመናዊና አረንጓዴ ከተማ በመሆን በእድገት ላይ ትገኛለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ በድርቅ የተመቱ አከባቢዎችን ወደ ለም መሬት በመቀየር፣ ማህበረሰብን መሰረት ያደረጉ የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ስራዎችን በመተግበር እና ከተግባራዊ ተሞክሮ በመነሳት የዓለም አቀፉን የኮፕ (ኮፕ) ጉባኤ በብቃት ለማስተናገድ ከፍተኛ አቅም እንዳላት ገልጸዋል።
የዓለም ባንክ የቀጣናዊ የአየር ንብረት አይበገሬነት ፕሮግራም (RCRP2) የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ የሆኑት ዩቮን ሱንዱ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ በሀገር ከ56 ቢሊዮን በላይ የዛፍ ችግኞችን በመትከል በተግባር የተደገፈ ስራ እየሰራች እንደሆነና ይህም እንደ ማላዊ ላሉ ለአደጋ ለሚጋለጡ ሀገራት ትልቅ አርዓያ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ማላዊ ያሉ የደቡብ ንፍቀ ዓለም ሀገራት የልማት አጋሮች እርዳታን ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ እንደ ኢትዮጵያ የመፍትሄ እርምጃዎችን መውሰድ አለባቸው ብለዋል።
የችግኝ ተከላ እና የታዳሽ ኃይል ልማትን ማስፋፋት ለአካባቢ ጥበቃ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የገነባችው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ያለውና በአፍሪካ ትልቁ የውሃ ኃይል ማመንጫ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም እንደ መሬትና የውሃ ሀብታቸው ሁኔታ ይህንን ተሞክሮ መቅሰምና ማስፋት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አፍሪካውያን አዎንታዊ ተሞክሮዎችን በመቅሰም ወደ ተግባር መሸጋገር እንዳለባቸው ገልጸው፣ በመጪው ኮፕ32 (COP32) ጉባኤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ምድር ስኬታማና በተግባር የተደገፈ ታሪካዊ ጉባኤ እንደምታዘጋጅ ትልቅ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በቱርክ ሀበርቱርክ ቲቪ (Habertürk TV) የዜና ዘጋቢ የሆኑት ኤምሬ ካራቻ ፣ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመከላከልና ለመቀነስ ወሳኝና አዎንታዊ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የምትከተለው አረንጓዴና ዘላቂ የልማት ጎዳና የህዝቧን መጻኢ እድል ብሩህ ከማድረጉ በላይ፣ የዓለም መሪዎችና ሌሎች ሀገራት ከኢትዮጵያ አስተዳደርና ተግባራዊ እርምጃዎች ተሞክሮ በመውሰድ በገዛ ሀገራቸው ሊተገብሩት የሚገባ አርዓያነት ያለው ስራ መሆኑን ተናግረዋል።