ቀጥታ፡

ኮፕ 31 ቃል ኪዳኖች ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚቀየሩበት የተግባር ጉባኤ ሊሆን ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30 /2019 (ኢዜአ)፦ 31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) በንግግርና በቃል ኪዳኖች ላይ ብቻ ሳይወሰን ተጨባጭ ውጤት የሚመጣበት የተግባር ጉባኤ መሆን እንዳለበት የኮፕ 31 ፕሬዝዳንትና የቱርኪዬ የአካባቢ፣ የከተማ ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ሙራት ኩሩም ገለጹ።

31ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤ (COP31) በቱርኪዬ አንታሊያ አስተናጋጅነት ዛሬ ተጀምሯል።

“ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት ወደተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን” የጉባኤው መሪ ቃል ነው።

በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ ተሳትፎ እያደረገች ትገኛለች።

የኮፕ 31 ፕሬዚዳንት ሙራት ኩሩም፣ ጉባኤው ቀደም ሲል የተገቡ የቃል ኪዳን ስምምነቶችን ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚቀይር (Implementation COP) እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

በአሁኑ ወቅት የጂኦፖለቲካ ውጥረቶች፣ የኢኮኖሚ አለመረጋጋትና እየከፋ የመጣው የአየር ንብረት ጉዳት ተደራራቢ ፈተናዎች እንደሆኑ መግለጻቸውን የቲአርቲ ወርልድ ዘገባ ያመለክታል።

የአየር ንብረት ፖሊሲ አሁን ላይ የልማት፣ የምግብ፣ የኢነርጂ፣ የከተማ ልማትና የጤና ፖሊሲ አካል መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ቱርኪዬ ኮፕ 31 በውይይት፣ በስምምነትና በተጨባጭ እርምጃዎች ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ትሻለች ያሉት ሚኒስትሩ የአንታሊያ ጥሪም ልዩነቶች በተበራከቱበት ወቅት በዚህ ወቅት ውይይትን ማሳደግ፣ የተሸረሸረውን እምነት ዳግም መመለስና የተገቡ ቃል ኪዳኖችን ከሕዝቦች የዕለት ተዕለት ሕይወት በማስተሳሰር መተግበር እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

በተጨማሪም ሚኒስትሩ እስከ እ.አ.አ 2035 ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል ከዓለም አቀፍ የኢነርጂ አጠቃቀም የሚይዘውን ድርሻ ወደ 35 በመቶ ለማሳደግ ያለመ "የ35-በ-35 ዓለም አቀፍ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ቃል ኪዳን" ይፋ አድርገዋል።

እንዲሁም ያደጉ ሀገራት በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት በየዓመቱ እስከ 300 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የአየር ንብረት ፋይናንስ ለማቅረብ የገቡትን ቃል ኪዳን እንዲፈጽሙ አሳስበዋል።

በጉባኤው የድርድር ሂደቱን በበላይነት እየመሩ ያሉት የአውስትራሊያ የአየር ንብረት ለውጥና ኢነርጂ ሚኒስትር ክሪስ ቦወን ናቸው።

ሚኒስትሩ አስቸኳይ እርምጃ ካልተወሰደ የዓለም ሙቀት መጨመር በፓሪስ ስምምነት ከተቀመጠው የ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ ገደብ ሊያልፍ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ይሁን እንጂ ሀገራት በአንድነትና በቁርጠኝነት ከተንቀሳቀሱ አሁንም የሙቀት መጠኑን ወደ ነበረበት መመለስ እንደሚቻል ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ለንጹሕ ኢነርጂ የተደረገው ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት 2.2 ትሪሊዮን ዶላር በመድረስ ከነዳጅና ከከሰል ዘርፍ በእጥፍ ቢበልጥም፣ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት አሁንም የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት እየተፈተኑ መሆናቸውን ቦወን ጠቁመዋል።

የአየር ንብረት ፋይናንስ ይበልጥ የሚያስፈልጋቸው ሀገራት አሁንም አነስተኛውን ድጋፍ እያገኙ መሆናቸውን በመጥቀስ ፍትሃዊና ፈጣን የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።

በዚህም መሰረት ሚኒስትሮቹ በተግባር ላይ ያተኮሩ የመፍትሔ እርምጃዎችን የሚያፋጥኑ ውሳኔዎች ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

ይህም በጉባኤው ወቅት ትኩረት የሚሰጣቸው ተግባራት በፍጥነት ወደ መሬት እንዲወርዱ ለማስቻል የተነደፈ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ኃላፊ ሲሞን ስቲል፤ ኮፕ 31 ግቦችን ከማስቀመጥ ባሻገር የታዳሽ ኢነርጂ አቅርቦትን ለማሳደግ፣ የኤሌክትሪክ አውታሮችን ለማጠናከር እና የሚቴን ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ አለበት ብለዋል።

በሚቴን ጋዝ መቀነስና በኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀም ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች ከታቀደው የአለም ሙቀት ላይ 0 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ ለመቀነስ እንደሚረዱም የቲአርቲ ዘገባ ያመለክታል።

31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) እስከ ህዳር 11 2019 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም