ጉዞ ወደ ታላቁ ስልጣኔ - ኢዜአ አማርኛ
ጉዞ ወደ ታላቁ ስልጣኔ
በመደመር እሳቤ የተበታተነ አቅምን ወደ ድርጁ ብሔራዊ አቅም በመቀየር፣ ጉዞ ወደ ታላቁ ስልጣኔ!
ኢትዮጵያ በታሪክ ድርሳኗ የከተበቻቸው መሪዎች ሀገሬ መልማት የምትችለው በምዕራቡ ወይም በምስራቁ የዓለም የፖለቲካ አካሄድ ነው በሚል በተውሶ አስተሳሰብ ሲያስተዳድሯት ቆይተዋል። ይህም ካላትና ከእውነቷ እንዳትነሳ በማድረግ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደቷ እና በስልጣኔዋ በብዙ ወደኋላ እንድትቀር አድርጓታል። የማደግ፣ የመለወጥ እና የመበልጸግ ተስፋዋን አመናምኖባት ቆይቷል።
በተለይ ኢትዮጵያ መለወጥ፣ ማደግ፣ መልማትና መሰልጠን አለባት ብለው በየጊዜው የተነሱ የለውጥ ሀይሎች መነሻቸውን እንጂ መድረሻቸውን በተገቢው ትንተና እና ስምምነት ባለመጀመራቸው የሰው ሀይል ከመብላትና ሀገር ከማቆርቆዝ የዘለለ ውጤት አለማምጣቱን ታሪካችን የከተበው ሀቅ ነው።
ይህ ማለት ግን በየዘመናቱ የነበሩ መሪዎች ሀገራችንን ለማሳደግ ምንም አልሰሩም ማለት አይደለም፤ በየዘመናቸው ለሀገር ይበጃል ያሉትን በርካታ ተግባራት አከናውነዋል። ቴክኖሎጂዎችንም ለማስተዋወቅ ጥረት አድርገዋል። በኢትዮጵያ ተበታትነው የሚገኙ አቅሞችን በማሰባሰብና ወደ አንድ ሀገራዊ ድርጁ አቅም በማምጣት ለሀገር ብልፅግና ማዋል ላይ ውጤታማ አልነበሩም ማለት እንጂ።
ኢትዮጵያ የታላቅ ታሪክ እና ህዝብ ባለቤት ብቻ ሳትሆን፣ የሚቆጩ ተቃርኖዎችንም ያስተናገደች ምድር ናት። እነዚህ ተቃርኖዎች በውስጣችን የሚፈጥሩት ስሜት ቁጭት ነው። ሀገራችን በራሷ መልማት፣ ማደግ፣ መበልጸግና መሰልጠን የምትችልባቸው በርካታ የታሪክ፣ የተፈጥሮ፣ የጂኦ-ፖለቲካ እና የሰው ኃይል ፀጋዎች ነበሯት፤ ዛሬም አሏት።
ታዲያ እነዚህን ፀጋዎች በማልማት ለምን ባለጸጋ መሆን አቃታት? የሚለው ጥያቄ በትክክል መመለስ አለበት። በተበታተነ አቅምና አቋም እንዲሁም ከዜሮ በመጀመር አባዜ የሚፈለገውን ዕድገትና ስልጣኔ እውን ማድረግ አይቻልም። የኢትዮጵያም ተደጋጋሚ የለውጥ ተስፋዎች የጨነገፉት በእነዚህ ምክንያቶች መሆኑን መጥቀስ ይቻላል። በየዘመናቱ ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ ነገሥታትም ሆኑ መንግሥታት፣ በነበራቸው ሀገር የማልማት መሻት የተለያዩ ጥረቶች ማድረጋቸው አይካድም። ትልቁ ክፍተት ግን ያንን አቅም ማሰባሰብና ወደ ድርጁ ብሔራዊ አቅም መቀየር አለመቻላቸው ነበር።
የመደመር እሳቤ በግልጽ እንዳስቀመጠው፣ ሀገር በአንድ ትውልድ፣ በአንድ መሪ ወይም በአንድ የአገዛዝ ሥርዓት ብቻ ተገንብታ አትጠናቀቅም፤ በትውልድ ቅብብሎሽ እንጂ። ለዚህ ነው የመደመር መንግሥት ወደኋላ መለስ ብሎ የታሪክ ስብራቶቻችንን በመፈተሽ ወረቶችን በመውሰድ የተፈጸሙ ስህተቶችን ለማረም እየተጋ የሚገኘው።
የመደመር መንግሥት በፍተሻው ከእያንዳንዱ የታሪክ ምዕራፍ በጎ ወረቶችን (እርሾዎችን) በማካተት፣ አዳዲስ አሰራሮችን፣ አቅሞችንና እሳቤዎችን በማከል አዲስ የዕድገት እና የስልጣኔ ጉዞ ከጀመረ ሰነባብቷል። በዚህም ባለፉት አመታት አስደማሚ ውጤቶችን አስመዝግቧል። አሁንም በጋራ እንሥራ፣ እንለወጥ፣ እንደግ፣ እንሰልጥን የሚል ሀገራዊ ጥሪውን ለሕዝብ እያቀረበ ይገኛል።
ከባከኑ የዕድገት ዕድሎች የሚወሰድ የቁጭት ትምህርት
ባለፉት አርባ እና ሃምሳ የኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ ውስጥ በርካታ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ለውጥ ዕድሎች ተፈጥረው እንደነበር ታሪክ ከትቦት እናገኛለን። ትልቁ ጥያቄ እነዚህን የለውጥ ዕድሎች ለሀገር ዕድገት ምን ያህል ተጠቀምንባቸው? የሚለው ነው። እንደ ሀገር እነዚህ የለውጥና የስልጣኔ ዕድሎች በሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ ባክነዋል መክነዋልም።
ለተገኙት የለውጥ ዕድሎች መባከን ዋነኛ ምክንያቶች፤ ለመሰረታዊ እና ግዙፍ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔዎች ከማስቀመጥ ይልቅ የአጭር ጊዜ መፍትሄ ላይ መተኮሩ እንደነበርም ታሪካችን ያመላክታል።
በተጨማሪም ያልተቀናጀ ትንተና ማለትም አካባቢያዊ፣ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ሁኔታዎችን በሚገባ መተንተን ላይ ክፍተት መታየቱ፣ ለውጡን ከሀገር የረጅም ጊዜ ዘላቂ ጥቅም ጋር አለማያያዛቸው፤ የእርምት ሳይሆን የማፍረስ ባህል ማለትም እያንዳንዱ አዲስ ለውጥ የቀደመውን በጎ ጅምር አፍርሶ ከዜሮ ለመጀመር መሞከሩ፤ በተጨማሪም ልዩነቶችን በጽንፈኝነት አስተሳሰብ በማስተናገድ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር አለመቻሉ መሆናቸውም ይጠቀሳል።
ትውልዱ በጋራ ሀገራዊ ልማት ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ በትናንት ታሪኮች ላይ በመቸንከር ባልተገባ አተካራና በትርክት ጦርነት ውስጥ ጊዜውን ሲያባክን መቆየቱም ለዚህ እንደ አንድ ምክንያት ተጠቃሽ ነው። ዛሬ ላይ ቆመን የምናየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጭት የመነጨውም ካለፈው ታሪክ ብቻ ሳይሆን፣ ካለን እምቅ አቅም እና ዛሬ ከምንገኝበት ዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ጭምር የሚመነጭ መሆኑ እሙን ነው።
ይህ የባከነ የዕድገት እና የስልጣኔ ጊዜ የሕዝባችን የቁጭት ምንጭ መሆን አለበት፤ ቁጭቱ ደግሞ ወደበጎ የልማት ኃይል ሊቀየር ይገባል። ካለፈው ውድቀት ትምህርት መውሰድ የነገ ስኬታችንን የሰመረ ያደርገዋል።
የተበታተነ አቅምን በመደመር ወደ ብሔራዊ ድርጁ ኃይል መለወጥ
መደመር ማለት በተናጠል የነበሩ፣ የተበታተኑና አቅጣጫቸውን የሳቱ የሀገር ውስጥ አቅሞችን በሙሉ በማሰባሰብ ወደ አንድ ድርጁ እና የማይበገር ኃይል ማሳደግ ማለት ነው። የኢትዮጵያን ዘላቂ ችግር ለመፍታት በመደመር እሳቤ መመራትና ሀገራችን ያሏትን እምቅ ጸጋዎች ወደ ልማት መቀየር፣ የተበታተኑ አቅሞችን ወደ ድርጁ ብሔራዊ አቅም ለማሳደግ ማተኮር ብቸኛው መንገድ ነው።
የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግር የማጣት ሳይሆን የመበታተን ችግር መሆኑ ይታወቃል። ለም መሬት፣ በርካታ ማዕድናት፣ ተስማሚ የአየር ንብረት፣ የረጅም ጊዜ ድልብ ታሪክና ቅርስ፣ አባይን ጨምሮ እጅግ ተጽዕኖ ፈጣሪ የውሃ ሀብትና ታታሪ ወጣት እያለን፣ የድህነት ተምሳሌት ሆነን የቆየንበት ምክንያት ፀጋዎቻችንንና አቅሞቻችንን አስተሳስረን መጠቀም ባለመቻላችን የመጣ መሆኑን የመደመር መንግሥት በሚገባ አስቀምጦታል።
እያንዳንዱ ዜጋ፣ እያንዳንዱ ክልል እና እያንዳንዱ የዕውቀት ዘርፍ ለየብቻው ከመንቀሳቀስ ወጥቶ አቅሙን ሲያቀናጅ፣ ኢትዮጵያ ማንም የማያቆማት የልማት ጉልበት ታገኛለች። ካለፉት ስምንት ዓመታት ወዲህ በመደመር መንግሥት የተከናወኑትና እየተከናወኑ የሚገኙት የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ የበጋ ስንዴ ምርት፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የቢሾፍቱ አየር ማረፊያ ግንባታ፣ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ፣ በቴክኖሎጂው ዘርፍ እየተመዘገቡ የሚገኙት ውጤቶች፣ የታዳሽ ኃይል ግንባታዎችና ሌሎች ግዙፍና ድርጁ ሀገራዊ አቅሞችን የሚፈጥሩ ፕሮጀክቶች የዚሁ የመደመር እሳቤ መገለጫዎች ናቸው።
የመደመር መንግሥት እሳቤ ለሀገራዊ ሁለንተናዊ ትንሣኤ
የመደመር እሳቤ ማለት ሀገር ያሏትን የተበታተኑ አቅሞች ወደ ድርጁ ኃይል በመቀየር የነገዋን ህብረ ብሔራዊ አንድነቷ የጠነከረ፣ የበለጸገች፣ የሰለጠነችና በአፍሪካ መሪ የሆነች ኢትዮጵያን የመገንቢያ ፍኖት ነው። ይህም የመላ ኢትዮጵያውያን የጋራ ርዕይ እውን የሚሆንበት መሳሪያም ጭምር ነው። የመደመር እሳቤ የሚከተሉትን ዋና ዋና የስልጣኔ ተስፋዎች ይዞም ተከስቷል፦ እነርሱም
ያለፉትን ስኬቶች መደመር ማለትም ካለፈው ታሪካችን በጎውን ወስዶ፣ ድክመቱን አርሞ፣ የዛሬውን አቅም አክሎ ለነገ ሥልጣኔ እንደ መነሻ መጠቀም፤ ሁለንተናዊ ብልፅግና ማለትም ሀገራችንን በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊ እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የላቀች ማድረግ፤ የትውልድ ቁርጠኝነት ማለትም እያንዳንዱ ዜጋ የባከኑ ጊዜያትን ሊያካክስ በሚያስችል መልኩ በቁጭት ተነሳስቶ ለታላቁ ግብ ስኬት በጋራ የሚቆምበትን አውድ ፈጥሯል።
ማጠቃለያ
ተቃርኖ ዘ-ኢትዮጵያ የወለደው ቁጭት ታሪካችንን የምንወቅስበት ሳይሆን፣ የወደፊት ዕድላችንን በጋራ የምንወስንበት የለውጥ ሞተር ነው። የተበታተኑ አቅሞቻችንን ወደ ድርጁ አቅም በመቀየር፣ በመደመር እሳቤ ጥላ ስር ሁላችንም በአንድነት መቆም ይጠበቅብናል። የነገዋ የበለጸገችና የሰለጠነች ኢትዮጵያ እውን የምትሆነው ዛሬ ሁላችንም ለጋራ ዓላማ በቁጭት ስንነሳ ብቻ መሆኑንም መገንዘብ ይገባናል።
በመሆኑም ሀገር የምትገነባው በትውልድ ቅብብሎሽ መሆኑን በውል በመገንዘብ እያንዳንዱ ዜጋ ቆም ብሎ ራሱን የሚከተሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች ሊጠይቅ ይገባል፦ እነርሱም ፦
1/ ካለፉት የባከኑ የዕድገትና የስልጣኔ ጊዜያት፣ እንደ ዜጋ መውሰድ ያለብኝ ትልቁ ትምህርት ምንድን ነው?
2/ የሀገራችንን እምቅ አቅም ወደ ድርጁ ብሔራዊ ኃይል ለመቀየር፣ እንደ ዜጋ አቅሜን ለመደመርና ሀገራዊ ግቦችን በጋራ ለማሳካት ምን እያደረግኩ ነው?
3/ በመደመር እሳቤ ጽንሰ-ሐሳብ የተበታተኑ አቅሞችን ወደ ድርጁ አቅም ለማሳደግ፣ በተሰማራሁበት የሙያ ዘርፍ ምን ዓይነት አስተዋጽዖ ማበርከት እችላለሁ? የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት ከራስ ጋር መመካከር እና በታሪክ የተገኘውን ይህን ዕድል በመጠቀም የራሳችንን አስተዋጽኦ ለማበርከት በቁጭት መነሳት ይገባናል።
በመደመር መንግሥት እሳቤ ጥላ ስር ሁላችንም በአንድነት በመሰባሰብ የነገዋን የበለፀገችና የሰለጠነች እንዲሁም ተጽእኖ የምትፈጥር ኢትዮጵያን እውን የምናደርግበት ትልቅ ዕድል ተፈጥሯል። "በአንድ እጅ አይጨበጨብም" እንዲል ብሂሉ ይህን ትልቅ ዕድል ወደ ተግባራዊ ስራ በመቀየር እንደ ሀገር የማደግ፣ የመልማት የመለወጥና የመሰልጠን ተስፋችንን እውን ማድረግ አለብን።