አረጋውያንን ማክበርና መደገፍ የሁሉም ማኅበረሰብ የጋራ ኃላፊነት ነው - ኢዜአ አማርኛ
አረጋውያንን ማክበርና መደገፍ የሁሉም ማኅበረሰብ የጋራ ኃላፊነት ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30 /2019 (ኢዜአ)፦አረጋውያን ለሀገር ጸንቶ መቆየት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ በመሆናቸው፣ እነርሱን ማክበርና መደገፍ የሁሉም ማኅበረሰብ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ልዕልቲ ግደይ ገለጹ።
መንግሥት ሀገር በትውልድ ቅብብሎሽ እንደምትገነባ በማመን፣ የዛሬ አረጋውያን ኢትዮጵያን ለማጽናት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ በማስገባት ተጠቃሚ የሚያደርጓቸውን በርካታ የልማት ተግባራት እያከናወነ ይገኛል።
በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ለአረጋውያን ምቹ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ፣ የሀገር ባለውለታዎች በመሆናቸው በሰው ተኮር የልማት ፕሮግራሞች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ36ኛ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ35ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ቀን "እንክብካቤና ዘላቂ ደህንነት ለአረጋውያን መልካም ሕይወት" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ከተማ በኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ ፓርክ ተካሂዷል፡፡
በዚሁ መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ልዕልቲ ግደይ፤ አረጋውያን ለሀገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በማስታወስ የዛሬዋ ኢትዮጵያ በቀደምት አባቶች ድካም፣ ትጋትና መሥዋዕትነት የተገነባች መሆኗን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑና እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ የሁሉንም ማኅበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን በልማት ውጤቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አረጋውያን የጀግንነት፣ የሀገር ፍቅርና የመልካም እሴቶች ተምሳሌቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ አዲሱ ትውልድ ከእነርሱ የሀገር ፍቅርን፣ ለሕዝብ የመሥራትን መርህና ለሀገር ኃላፊነት የመወጣትን እሴት መማር እንዳለበት አሳስበዋል።
በከተማዋ በተገነቡ "የተስፋ ብርሃን" የምገባ ማዕከላት ድጋፍ የሌላቸውን አረጋውያን በየቀኑ ቢያንስ አንድ ጊዜ ምግብ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማትና ሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታዎችም የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር በተጨማሪ፣ ለአረጋውያን ምቹና ተስማሚ አካባቢ ለመፍጠር ያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የአረጋውያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ክፍሉ በበኩላቸው፣ አረጋውያንን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችና እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።
አረጋውያን መሥራትና ለራሳቸው ገቢ ማስገኘት ይችላሉ በሚል ጽኑ እምነት፣ አቅማቸውን በሚመጥኑ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች እንዲሰማሩ እየተደረገ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
የአውራ አምባ ማኅበረሰብ መሥራችና መሪ ዙምራ ኑሩ በሰጡት አስተያየት፣ ሰዎች በፍቅርና በአንድነት መኖር እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት የአንድ ጊዜ ተግባር ሳይሆን፣ በቀጣይነትና በተደራጀ መልኩ መፈጸም ያለበት ማኅበራዊ ኃላፊነት መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም የታችኛውን የመንግሥት መዋቅሮች በመጠቀም ጭምር ለአረጋውያን አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ሥርዓት ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
በመድረኩ የተገኙት አረጋዊ አቶ ግርማ ከበደ በበኩላቸው፣ በአዲስ አበባ ከተማ በተከናወነውና እየተከናወነ በሚገኘው የኮሪደር ልማት አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል።