ቀጥታ፡

ኮፕ 31 ለኮፕ 32 አዘጋጅነታችን የኢትዮጵያን ዝግጁነት ለዓለም የምናሳይበት ትልቅ መድረክ ነው - ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30 /2019 (ኢዜአ)፦ ኮፕ 31 ኢትዮጵያ ለኮፕ 32 ያላትን ዝግጁነት ለዓለም የምታሳይበት ትልቅ መድረክ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ዋና ተደራዳሪ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) ዛሬ በቱርኪዬ አንታሊያ ተጀምሯል።

“ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት ወደተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን” የጉባኤው መሪ ቃል ነው።

የገንዘብ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተደራዳሪ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በኮፕ 31 ስለሚኖራት ንቁ ተሳትፎ እና በኮፕ 32 የድርድር ቅድመ ዝግጅት ሂደት እየተከናወነ ስላለው የአቅም ግንባታ ሥራ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ አዲስ አበባ የምታስተናግደው 32ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) ከመደረጉ በፊት የሚካሄደው ይሄው የኮፕ 31 ጉባኤ ኢትዮጵያ ዝግጅቷን በጠንካራ ሁኔታ መጀመሯን እና ዓለምን ለማስተባበርና ለመደራደር ያላት አቅም የሚታይበት ትልቁ መድረክ ነው።

በድርድሩ የኢትዮጵያን አቋም ብቻ ሳይሆን፣ ዓለምን ወክሎ ጠንካራ የድርድር ውጤቶችን በሰነዶች ውስጥ ለማካተት ከወዲሁ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በጉባኤው ማዕቀፍ ውስጥ ኢትዮጵያን በሰፊው የሚያስተዋውቅ፣ ኢንቨስትመንት የሚስብ፣ አጋርነት የሚፈጠርበት የቡና እና የሰው ዘር መገኛ መሆኗን የሚያሳይ ግዙፍ ፓቪሊዮን መከፈቱንም ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ከአፍሪካ የተደራዳሪዎች ቡድን፣ ከታዳጊ አገሮች፣ ከቻይና፣ ከቡድን 77 እና ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ሰፊ ውይይቶች እንደሚደረጉ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተጋላጭነት ቢኖራትም፣ የራሷን እርምጃዎች በቁርጠኝነት እየወሰደች መሆኗንም ነው የገለጹት ዋና ተደራዳሪዋ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ የሆነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ ከ90 በመቶ በላይ የደረሰው ንጹህ የሃይድሮ ኢነርጂ አጠቃቀም፣ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን ለማበረታታት የተወሰዱ እርምጃዎች እና በግብርናና ከተማ ልማት የተከናወኑ ተግባራት ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እምነትና አድናቆት እንዳተረፉላት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም