ቀጥታ፡

የኢትዮ-ኮደርስ ሥልጠና ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለአገልግሎት ቅልጥፍና አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

ሀረር፤ ጥቅምት 30/2019 (ኢዜአ)፡- የአምስት ሚሊዮን የኢትዮ-ኮደርስ ሥልጠና የዜጎችን የዲጂታል ክህሎት በማዳበር ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለአገልግሎት መቀላጠፍ ከፍተኛ አስተዋጽአ እያበረከተ መሆኑ ተገለጸ።

ዘርፉን በእውቀት ለመምራት የአሰራርና የፖሊሲ ማዕቀፎች ተቀርጸውለት ወደ ተግባር በመገባቱ ውጤት እየተመዘገበበት እንደሚገኝም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በጉዳዩ ላይ በሐረሪ ክልል ስልጠናውን የወሰዱ የህብረተሰብ ክፍሎችና የሥራ ኃላፊዎችን አነጋግሯል።

የሐረር አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የባዮሎጂ መምህር አንባዬ ፍቅሬ እንደገለጹት፤ በኢትዮ-ኮደርስ ሥልጠና ያገኙት ክህሎት ሥራቸውን  ወቅቱ በደረሰበት ቴክኖሎጂ በመጠቀም ይበልጥ ውጤታማ  ለማድረግ  አስችሏቸዋል። 

በተለይም  ሰው ሰራሽ አስተውሎትን (AI) በመጠቀም የመማር ማስተማር ሥራቸውን  ለማከናወን ከፍተኛ እገዛ እንዳደረገላቸው አንስተዋል።


 

ሥልጠናው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እውቀቱን ለማዳበር እንደረዳው የገለጸው ደግሞ ወጣት ዮሴፍ አብዱረሃማን ነው።

ሥልጠናው የንድፈ-ሐሳብ እውቀቱን  በተግባር የሚያውልበትን ክህሎት  ለማዳበርና በሥራ ገበያው ላይ ያለውን ተወዳዳሪነት ለመጨመር እንደጠቀመው አስረድቷል።


 

የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ሱመያ አማን በበኩሏ፥ የኢትዮ-ኮደርስ ሥልጠና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎቷን በማሳደግ በትምህርቷ ውጤታማ የምትሆንባቸውን መረጃዎች ይበልጥ የምትጠቀምበትን ዕድል እንደፈጠረላት ጠቁማለች። 

በመሆኑም ሌሎች ወጣቶችና ተማሪዎች ዕድሉን እንዲጠቀሙበት ከልምዷ በመነሳት መክራለች።

የሐረሪ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ጀማል ኢብራሂም በበኩላቸው፤ በክልሉ የ5-ሚሊዮን ኮደርስ ሥልጠና የወጣቶችን የቴክኖሎጂ አቅም በማሳደግና የሥራ ፈጠራ ዕድሎችን በማስፋፋት ረገድ ትልቅ አቅም እየሆነ ነው ብለዋል።


 

ለዚህም ማሳያ በክልሉ ሥልጠናውን በአግባቡ ካጠናቀቁ ከ55 ሺህ በላይ ዜጎች ውስጥ ከ41 ሺህ በላይ የሚሆኑት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የምስክር ወረቀት ማግኘት መቻላቸውን አመልክተዋል።

በክልሉ ያሉ ወጣቶች ሥልጠናውን ወስደው በቀጥታ ወደ ሥራ እንዲገቡ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም  ኃላፊው ጠቁመዋል። 

ተግባሩን አጠናክሮ ለማስቀጠል በበጀት ዓመቱ 20 ሺህ የሚሆኑ አዳዲስ ወጣቶችን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ መተግበሪያ ማበልጸግ (Android Development)፣ በዳታ ሳይንስና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲጨብጡ ለማድረግ  ወደ ሥራ መገባቱን አስታውቀዋል። 

ኢትዮ-ኮደርስ ሥልጠና በክልሉ የመንግሥት አገልግሎትን ቀልጣፋ፣ ግልጽና ተደራሽ ለማድረግ ጭምር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አክለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም