ኢትዮጵያ በኮፕ 31 የምታከናውናቸው ስራዎች ለኮፕ 32 ስኬት ትልቅ አቅም ይፈጥራል-ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በኮፕ 31 የምታከናውናቸው ስራዎች ለኮፕ 32 ስኬት ትልቅ አቅም ይፈጥራል-ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30 /2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በኮፕ 31 የምታከናውናቸው ስራዎች ለኮፕ 32 ስኬት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) ዛሬ በቱርክዬ አንታሊያ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
“ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት ወደተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን” የጉባኤው መሪ ቃል ነው።
በጉባኤው ላይ የሀገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተደራዳሪዎች፣ የግሉ ዘርፍ እና የሲቪክ ማህበራትን ጨምሮ ከ60 ሺህ እስከ 100 ሺህ የሚገመት ልዑክ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያም በጉባኤው ላይ ተሳትፎ እያደረገች ይገኛል። በጉባኤው የኢትዮጵያ ይፋዊ ፓቪሊዮን (Pavilion) በይፋ ተከፍቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ፓቪሊዮንን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ የኮፕ 32 አስተናጋጅ በመሆኗ በዚኛው ጉባኤ ማሳካት የምትፈልጋቸው ግቦች እንዳሉ ገልጸዋል።
በኮፕ 31 የሚደረጉ ድርድሮች ውጤታማ በማድረግ በኮፕ 32 ወቅት የተሻለ መደላድልን መፍጠር እና መሰረት ለመጣል እንደሚሰራ አመልክተዋል።
ለዚህም ከቱርኪዬ እና አውስትራሊያ ጋር የትብብር ስራዎች እንደሚከናወኑም አመልክተዋል።
በፓቪሊዮኑ የሚደረጉ በርካታ ውይይቶች ላይ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ በመከላከል ረገድ እያከናወነች ያለውን ስራ በስፋት እንደሚቀርብም ጠቅሰዋል።
አጋርነት ማስፋት እና ኮፕ 32 የበለጠ ሰዎች እንዲጠብቁት እና በርካታ ልዑካን እንዲሳተፉ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግም ጠቅሰዋል።
ለኮፕ 32 ዝግጅት ተግባራዊ ስራዎች መጀመራቸውንና ለዚህም የተዋቀረው ቡድን ልምድ የመቅሰም ተግባር እንደሚከናወን ተናግረዋል።
ለተሞክሮ እና ልምድ ልውውጥ መድረኩ ውጤታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላደረጉት ለብራዚል የኮፕ 30 ፕሬዝዳንት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።