ቀጥታ፡

የጤና ዘርፉን በማዘመንና ተደራሽነትን በማስፋት የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው

ሆሳዕና ፤ ጥቅምት 30/2019 (ኢዜአ) ፦ የጤና ዘርፉን በማዘመንና ተደራሽነትን በማስፋት ፈጣንና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።

28ኛው የጤና ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳእና ከተማ የተካሄደ ሲሆን ከጉባኤው በተጓዳኝ የጤና ተቋማት ተጎብኝተዋል።

ከጉባኤው ታዳሚዎች መካከል የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ፤ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ አሁን ላይ እጅግ እየዘመነ እና እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።


 

እንደ ሀገር በሽታን የመከላከልና አክሞ የማዳን ስትራቴጂ በመከተል ለዜጎች የተሻለ አገልግሎት የመስጠት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።

በመሆኑም የጤና ዘርፉን በማዘመንና ተደራሽነትን በማስፋት ፈጣንና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም ይህንኑ የሚያመላክቱ አገልግሎቶችን አይተናል ያሉት ዶ/ር ሰላማዊት፤ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ዘመናዊ አሰራርን አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን አጽኖት ሰጥተዋል።


 

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አብድልከሪም መንግስቱ፤ የጤና ተቋማትን ዲጅታላይዝ በማድረግና ቀልጣፋ አሰራሮችን በመዘርጋት ለዜጎች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወራቤ  ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጉብኝት የተመለከቱት ይህንኑ የሚያረጋግጥና ጥሩ ተሞክሮ የተወሰደበት መሆኑንም ተናግረዋል።


 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ ሳሙኤል ዳርጌ፤ በክልሉ የህክምና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሻሻል የተጀመሩ ጥረቶች ውጤት እያመጡ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም የህክምና ተቋማትን በቁሳቁስና ግብአቶች የማሟላት ብሎም ዘመናዊ አሰራርን የመዘርጋት ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል። 

 

 

 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም