ለአፍሪካ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት የትምህርት ሥርዓቱን ማጠናከር ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለአፍሪካ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት የትምህርት ሥርዓቱን ማጠናከር ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 30/2019 (ኢዜአ)፡-የትምህርት ሥርዓትን ማጠናከር ለአፍሪካ ዘላቂ ልማት፣ ለኢኮኖሚ ለውጥና ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት መሠረታዊ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሰሎሞን አብርሃ (ዶ/ር) ገለጹ።
በኢትዮጵያ የ23ኛውን የሒሳብ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ትምህርት አፍሪካ አቀፍ ኮንፍረንስ (COMSTEDA) የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሰሎሞን አብርሃ (ዶ/ር)፤ ትምህርት ከዕውቀት ማስተላለፍ ባለፈ ሳይንሳዊ ምርምርን፣ ጥልቅ አስተሳሰብንና ችግር ፈቺነትን ማዳበር እንዳለበት አሳስበዋል።
በተለይም እንደ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና ሮቦቲክስ ያሉ የታዳጊ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ወጣቱን ለወደፊት የሥራና የልማት ዕድሎች ለማዘጋጀት ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የመምህራንን ሙያዊ እድገት፣ የሥርዓተ-ትምህርት ዘመናዊነትን፣ ዲጂታል ትምህርትንና የላቦራቶሪ መገልገያዎችን ለማጠናከር የማያቋርጥ አስተዋጽኦ ስታደርግ መቆየቷን ገልጸዋል፡፡
ማንኛውም ተማሪ የሥርዓተ-ፆታ፣ የአካል ጉዳት ወይም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዳራ ሳይገድበው እኩል ዕድል ማግኘት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ በበኩላቸው፤ የተማሪዎችን የማሰብ፣ የመመራመርና የፈጠራ አቅም ማጎልበት በአፍሪካ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት ላይ የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስረድተዋል።
በአፍሪካ የትምህርት ስርዓቱ በግብርና፣ በንጹህ ኃይል፣ በጤና፣ በውሃ አስተዳደርና በኢንዱስትሪ ዘርፎች የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት የሚችሉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቁመው፣ ትምህርቱን ከሀገራዊ የልማት ቅድሚያ ጉዳዮች ጋር ማገናኘት እንደሚገባ አስረድተዋል።
ተማሪዎች የአካባቢያቸውን ችግሮች በመመርመር፣ ሙከራ በማድረግና መፍትሄዎችን በመፍጠር ተግባራዊ እውቀት እንዲያዳብሩ ማበረታታት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
አካዳሚው በሳይንስና ሒሳብ ማዕከላት፣በሳይንሳዊ ውይይቶች ፣ በፌስቲቫሎችና በተንቀሳቃሽ የሳይንስ ኤግዚቢሽኖች ተማሪዎች ሳይንሳዊ እውቀትን በተግባር እንዲለማመዱ እድሎችን እያመቻቸ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ የሒሳብና የሳይንስ ትምህርት ማኅበር ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ቤንሰን ባንዳ፤ የአፍሪካን የወደፊት ዕድል ለመቀየር ትምህርትን ከሥርዓተ-ትምህርት ሽፋን ባሻገር ተማሪዎች በተግባር እንዲመረምሩና ችግሮችን እንዲፈቱ በሚያስችል መልኩ ማሻሻል እንደሚገባ ተናግረዋል።
አፍሪካ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ተጠቃሚ ብቻ ሳትሆን የራሷን የቴክኖሎጂ ሞዴሎችና የፈጠራ ሥራዎች ማዳበር እንዳለባት በመጠቆም፣ አህጉራዊ ትብብርን በማጠናከርና በመምህራን ላይ በሚደረግ ኢንቨስትመንት አህጉሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብትና የወጣት ኃይል ወደ እውነተኛ የልማት አቅም መለወጥ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ የዩኔስኮ ተወካይ ሪታ ቢሱናት (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የአፍሪካን የሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅም ለማጎልበት ጥራት ያለውና አካታች የሳይንስና ሂሳብ (ስቲም) ትምህርትን ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ወጣቶች የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆኑ የእውቀትና የፈጠራ ምንጭ እንዲሆኑ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በሙያ ክህሎት ላይ ማተኮር እንዳለበት አስረድተዋል።
የዩኔስኮ በዲጂታል ትምህርት፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና በሳይንስ የሴቶች ተሳትፎ ማበረታታት ላይ ድጋፉን እያጠናከረ መሆኑን ጠቁመው፣ የአፍሪካን የሳይንስና ትምህርት እድገት ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያና ከአህጉራዊ አጋሮች ጋር በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።