የአረንጓዴ ዓሻራ ስኬት በኮፕ 31 መድረክ - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ዓሻራ ስኬት በኮፕ 31 መድረክ
31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) ዛሬ ቡርኪዬ አንታሊያ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
“ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት ወደተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን” የጉባኤው መሪ ቃል ነው።
በጉባኤው ላይ የሀገራት መሪዎች፣ሚኒስትሮች፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተደራዳሪዎች፣ የግሉ ዘርፍ እና የሲቪክ ማህበራትን ጨምሮ ከ60 ሺህ እስከ 100 ሺህ የሚገመት ልዑክ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያም በጉባኤው ላይ ተሳትፎ እያደረገች ይገኛል።
በጉባኤው የኢትዮጵያ ይፋዊ ፓቪሊዮን (Pavilion) በይፋ ተከፍቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) እንዲሁም የፋይናንስ ሚኒስትርና የኮፕ 32 ዋና ተደራዳሪ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ታድመዋል።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ ያከናወነቻቸውን ስራዎች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተሞክሮነት ታቀርባለች።
በተሞክሮነት ከሚቀርቡ ስራዎች መካከል አረንጓዴ ዓሻራ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው አረንጓዴ ዓሻራ እስካሁን ባለው ሂደት ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።
አረንጓዴ አሻራ በአፍሪካ ትልቅ የአካባቢ ጥበቃና የተፈጥሮ ማገገሚያ ፕሮግራም ነው።
ይህ ንቅናቄ የሀገሪቱን የደን ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ፣ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ለማልማት እና የውሃ ተፋሰሶችን ለመጠበቅ ያስቻለ ሰፊ የሕዝብ ተሳትፎ የታየበት ሥራ ነው።
በጉባኤው ላይ የሚቀርበው ይህ ተሞክሮ፣ የአየር ንብረት መዛባትን ለመቋቋም በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት እያከናወኑት ላለው ስራ ተሞክሮ የሚሆን ነው።
የአረንጓዴ ዓሻራ መርሐ ግብሩ ከተፈጥሮ ጥበቃ ባለፈ ከሀገሪቱ የዘላቂ ልማትና ታዳሽ ኃይል ግንባታ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው።
በችግኝ ተከላና በተፋሰስ ልማት ሥራዎች አማካኝነት የአፈር መሸርሸርን መቀነስ መቻሉ፣ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ የውሃ ኃይል ማመንጫዎች ዘላቂ የውሃ ፍሰት እንዲኖራቸውና ከደለል መከማቸት እንዲጠበቁ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ይህም ኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦቷን ከንጹሕና ታዳሽ ምንጮች የማመንጨት ሀገራዊ ግቧን እንድታሳካና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሽግግሯን በተግባር እንድታረጋግጥ መሠረት ሆኗታል።
ኢትዮጵያ በአንታሊያ የምታቀርበው የአረንጓዴ ልማት ተሞክሮ፣ የኮፕ 32 አስተናጋጅነቷ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ማዕከል እንድትሆን በር የሚከፍት ነው።
31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) እስከ ህዳር 11 2019 ዓ.ም ይቆያል።