በክልሉ ሰላምን በዘላቂነት ለማጽናትና ልማትን ለማፋጠን በሚከናወኑ ተግባራት የበኩላችንን እንወጣለን- የኃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ሰላምን በዘላቂነት ለማጽናትና ልማትን ለማፋጠን በሚከናወኑ ተግባራት የበኩላችንን እንወጣለን- የኃይማኖት አባቶች
ጋምቤላ፤ ጥቅምት 30/2019 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል ሰላምን በዘላቂነት ለማጽናትና ልማትን ለማፋጠን በሚከናወኑ ተግባራት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የኃይማኖት አባቶች ገለጹ።
የክልሉ የኃይማኖት ተቀማት ጉባኤ ህዝባዊ የሰላም የእግር ጉዞ መርሃ ግብር ዛሬ በጋምቤላ ከተማ አካሂዷል።
የኃይማኖት አባቶች በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ሰላም ለሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ሰላምን በዘላቂነት ማጽናት የሁሉም ሀላፊነት ሊሆን ይገባል።
በተለይ የኃይማኖት ተቋማት ምዕመናንን በማስተማር ጭምር በክልሉ ሰላምን አጠናክሮ ለማስቀጠል ኃላፊነታቸውን በበለጠ ሊወጡ እንደሚገባ አመላክተዋል።
የጋምቤላ ክልል ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ፕሬዚዳንትና የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ቄስ ኝጎዎ አሞድ እንዳሉት፣ ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት የበኩላቸው እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በተለይ የህብረተሰቡ በጋራ አብሮ የመኖር እሴቶችን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ተባብረን ልንሰራ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጋምቤላ ሀገረ ስብክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ተዘራ ዋቅጋሪ በበኩላቸው፣ ለክልሉ ዘላቂ ሰላም ሁላችንም በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል።
በአካባቢው ሰላምን በዘላቂነት ማስፈን ከተቻለ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ልማትና እድገትን ለማሳካት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።
ለክልሉ ልማት መፋጠን ሰላም ዋነኛ መሰረት መሆኑን ያነሱት ደግሞ የጋምቤላ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ኡስታዝ ኡስማን ኡመር ናቸው።
የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ቱት ጆክ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የኃይማኖት አባቶች በሰላም ግንባታ ሂደት ላይ የማይተካ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል።
በመሆኑም ለክልሉ ሰላምና ልማት መረጋገጥ የሚያደርጉትን አስተዋጾ ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በሰላም የእግር ጉዞ መርሃ ግብሩ ላይ የጋምቤላ ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።