የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ፡የሥልጣኔና የታሪክ ምሉዕነትን የማደስ ጉዞ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ፡የሥልጣኔና የታሪክ ምሉዕነትን የማደስ ጉዞ
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት፣ በአፍሪካ የኢኮኖሚና የጂኦ-ፖለቲካዊ መረጋጋት ዋና መሠረት የሆነችው ኢትዮጵያ፣የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የሕልውና እና ታሪካዊ ፍትሕን የማስፈን ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ያላት ቁርኝት ጥንታዊና በታሪክ የተረጋገጠ እውነት ነው።በጥንታዊው የአክሱም ሥልጣኔ ዘመን አዱሊስ ዋና የወደብ ከተማ በመሆን ኢትዮጵያን ከሜዲትራኒያን፣ ከእስያና ከሕንድ ጋር ያገናኘችበትና የቀይ ባሕር ንግድን በበላይነት ይመራ የነበረበት የታሪክ ምዕራፍ ነበር።
በመካከለኛው ዘመንም ቢሆን የኢትዮጵያ ነገሥታት የቀይ ባሕር ዳርቻዎችንና ደኅንነትን የሚቆጣጠር የባህር ነጋሽ አስተዳደር በመሾም የሀገሪቱን የማሪታይም ባለቤትነት አስከብረው ቆይተዋል።
ሆኖም ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል ከተደረገ በኋላ፣ ዓለም አቀፍ ሕግ ለቀድሞ የባሕር በር ባለቤቶች የሚሰጠውን ፍትሃዊ መብት ችላ ተብሎ፣ ኢትዮጵያ ያለ ምንም የባሕር በር አማራጭ የመልክአ ምድር እስረኛ እንድትሆን ተደርጋለች።
ይህን ተከትሎ ሀገሪቱን ለከፍተኛ የኢኮኖሚና ስትራቴጂካዊ ተግዳሮቶች ተጋላጭነት ዳርጓታል።የኢትዮጵያ ፍትሐዊ ጥያቄ በዓለም አቀፉ የባሕር ሕግ ኮንቬንሽን (UNCLOS) መርሆዎች ላይ የተደገፈ ቢሆንም፣ አንዳንድ የቀጣናው ሀገራት ግን ይህንን እውነታ በመካድ እኩይ አላማቸውን ለማስፈጸም ሲታትሩ ይስተዋላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት ምስረታ ወቅት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ ዘመናዊነትና ሥልጣኔ ያለ ባህር በር ሊታሰብ አይችልም፤ በመሆኑም በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ የባህር መግቢያ በር እንድታገኝ በቁርጠኝነት እንሠራለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጥያቄ የሌሎችን ሀገራት ሉዓላዊነትና የድንበር አንድነት የሚጋፋ የኃይል አማራጭ ሳይሆን፣ በጋራ ተጠቃሚነትና በሰላማዊ ድርድር ላይ የተመሠረተ መሆኑን ነው። ፈጣን የሕዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ ዕድገትና ቀጣናዊ የሰላም ሁኔታዎች የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ይበልጥ አንገብጋቢ ያደርገዋል።
የኢትዮጵያን ከመልክዐ ምድር እስረኛነት ማነቆ ማላቀቅ የህልውና ጉዳይ ከመሆኑም በላይ የባህር በር ባለቤትነት ለኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ፋይዳ ያለው ሀብት ነው።
በቀይ ባህርና በባብ ኤል ማንዳብ ወሳኝ የንግድ መስመር ላይ የውጭ ኃይሎች ወታደራዊና ስትራቴጂካዊ ተጽዕኖ እያደገ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ በቀጣናው ትልቅ የሕዝብ ቁጥርና የደኅንነት አቅም ያላትን ኢትዮጵያ ከባሕር በርና ጉዳይ አገላለሁ ማለት የቀጣናውን ዘላቂ ሰላምና የጂኦ-ፖለቲካዊ ሚዛን አደጋ ላይ መጣል ነው።
ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ቀጣና ንቁ ተሳትፎ ማድረጓና የባህር በር ማግኘቷ ለአንድ ሀገር ጥቅም ብቻ ሳይሆን፣ ዓለም አቀፍ የንግድ መስመሩ አስተማማኝ ጥበቃ እንዲኖረው፣ ቀጣናዊ መረጋጋት እንዲሰፍንና የቀይ ባህር ቀጣና የሀገራት የመፋለሚያ ከመሆን እንዲድን ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችል አቅም ይፈጥራል።
ኢትዮጵያን የመልክዐ-ምድር እስረኛ አድርጎ በማስቀረት የቀጣናውን የኢኮኖሚና የጂኦ-ፖለቲካዊ የበላይነት መቆጣጠር የግብጽና መሰሎቿ ፋላጎት ሲሆን ይህ አካሄድ በታሪክም ሆነ በሕግ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ነው።
የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ታሪካዊና ፍትሐዊ መብትን በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ የማረጋገጥ ጉዞና የትኛውም ኃይል ሊያስቆመው የማይችለው የኢትዮጵያውያን የትውልድ የማይታጠፍ ብሔራዊ ጥያቄ መሆኑም መገንዘብ ይገባል።