በሶማሌ ክልል የግብርና ምርታማነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት እየተመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል የግብርና ምርታማነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት እየተመዘገበ ነው
ጂግጂጋ፣ ጥቅምት 29/2019 (ኢዜአ)፡-በሶማሌ ክልል የግብርና ምርታማነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ግብርና ቢሮ የኤክስቴንሽን ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሕመድ መሐመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በ2018/2019 የምርት ዘመን ከ2 ሚሊዮን 11 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ61 ሚሊዮን 223 ሺህ በላይ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ በስፋት እየተሰራ ነው።
በዚህም የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመውጣትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
የመደመር መንግስት ለግብርና ልማት ሥራ የሰጠውን ትኩረት ተከትሎ በክልሉም ምርታማነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
የመኸር ወቅት የግብርና ዕቅድን ስኬታማ ለማድረግም 7ሺህ 200 ኩንታል ምርጥ ዘር እና 8 ሺህ 816 ኩንታል የአትክልት ዘር ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱን አስታውቀዋል።
በክረምት ዝናብ መቀነስ ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን የምርት እጥረት ለማካካስ የበጋ መስኖ ልማት ዝግጅት በስፋት መጀመሩን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ የግብርና ምርታማነት ዕቅዱን ለማሳካትም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፣ የባለሙያ ድጋፍና የቅርብ ክትትል ሥራ መጠናከሩን ጠቁመዋል።
በቢሮው የአነስተኛ መስኖ ጥናትና ዲዛይን ቡድን መሪ አቶ መሀድ ኑር በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በክልሉ የበጋ መስኖ ግብርናን ይበልጥ ለማስፋፋት 14 የመስኖ ልማት አውታሮች ሥራ ላይ ውለዋል።
የመስኖ አውታሮቹ በአጠቃላይ 1ሺህ 820 ሄክታር መሬት እንደሚያለሙ ገልጸው፣ ሥራውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ 198 የውኃ መሳቢያ ጄነሬተሮች ለአርሶ አደሮች መሰራጨታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ከ9 ሺህ 600 በላይ አርሶ አደሮች በቀጥታ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።