ቀጥታ፡

የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ለቀይ ባህር ቀጣና የጋራ እድገት አስተዋፅዖው የላቀ ነው-ምሁራን 

ድሬዳዋ፣ ጥቅምት 29/2019 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ለቀጠናው ዘላቂ ሰላምና የጋራ ዕድገት የላቀ አስተዋፅኦ እንዳለው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዋኬና ዓለማየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ታሪካዊና ሕጋዊ መሠረት ያለው፣ የትውልዱ ትክክለኛ የህልውና አጀንዳ ነው።

ይህ ጥያቄ  መፍትሔ እንዲያገኝ እየተደረገ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

ምሁራንም በጥናትና ምርምር የታገዙ እውነቶችን ለዓለም ማኅበረሰብ ተደራሽ በማድረግ የባህር ባለቤትነት ጥያቄው ፈጣን ምላሽ እንዲያገኝ እገዛ ማድረግ አለበን ያሉት መምህሩ፣ ለዚህም የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን አረጋግጠዋል። 

የባሕር በር ጥያቄ  ምላሽ ማግኘት ከኢትዮጵያ ባለፈ ለቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ለጋራ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ የጎላ መሆኑንም መምህር ዋኬና አስረድተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የታሪክና የቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ቦንሳ አዱኛ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ለማስመለስ የተጀመሩ ሁለንተናዊ ጥረቶች የአካዳሚውን ማኅበረሰብ የነቃ ተሳትፎ ይፈልጋሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ህጋዊም ሆነ ታሪካዊ አመንክንዮ ያላት በመሆኑ እስኪሳካ ድረስ መንግስትና ዜጎች የጀመሯቸውን ጥረቶች ማጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ አሳማኝ መረጃ በሌለበት ሁኔታ በሕገ-ወጥ መንገድ ከባሕር በሯ በሴራ እንድትገለል የተደረገበት መንገድ የትውልድ ሁሉ ቁስል ነው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የታሪክና የቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ሁለመናይ ለገሰ ናቸው።

ያለአግባብ ያጣቸውን የባህር በር ለማስመለስ ህዝብና መንግስት የሄዱበት ርቅት የሚበረታታ መሆኑንም ነው የገለጹት።

 ጉዳዩን በዘላቂነት ለማሳካት ምሁራን በተሰማሩበት የሙያ መስክ ሁሉ አበርክቷቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ምሁሩ መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም