ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የተመዘገቡ ሁለንተናዊ የልማት ስኬቶች የሚደነቁ ናቸው  

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29/2019 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የልማት፣ የዲጂታላይዜሽን እና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስኬቶች ለአፍሪካ ዘላቂ ብልፅግና አርዓያ የሚሆኑና የሚደነቁ  መሆናቸውን ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ እንግዶች ገለጹ።

"ዕድገትን መምራት፤ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየውን ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ትናንት ተጠናቋል።

በጉባኤው ተሳታፊ የነበሩ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች በመዲናዋ የተከናወኑ የልማት ስራዎችና የተመዘገቡ ውጤቶችን ጎብኝተዋል።

ተሳታፊዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት በኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት፣ በከተማ ጽዳትና አረንጓዴ ልማት፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የሚታዩ ለውጦች የሚደነቁ ናቸው።

እንዲሁም በወጣቶች አቅም ግንባታ የተመዘገቡ ስኬቶች ለአፍሪካ ትልቅ ትምህርት የሚሰጡ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል የኬንያ ተመራማሪ ማርቲን ቡሩ እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራቸው ልማት ጉዳይ በጋራ መስራታቸው አርዓያ የሚሆን ነው።

በኢትዮጵያ በከተሞች ውበት፣ በመንገድ መሰረተ ልማት እና በግድብ ግንባታ ዘርፎች የታዩት ለውጦች የሚያስደምሙ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗ አህጉራዊ ውህደትን ለማጠናከር የምታደርገው ጥረት ከፍተኛ መሆኑን ተመልክቻለሁ ብለዋል።

ከኡጋንዳ የመጡት የፓርላማ አባል ኛካቶ አሲናንሲ ካማንዳ በበኩላቸው፤  አዲስ አበባ እጅግ ጽዱ፣ የለማችና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም በአረንጓዴ ልማት የተሸፈነች ውብ ከተማ መሆኗን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ፈጣን ሽግግር እያደረገ መሆኑ አፍሪካውያን በራሳቸው አቅም የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን እውን ማድረግ እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

አፍሪካውያን ከውጭ ብድር እና እርዳታ ጥገኝነት ወጥተው በጋራ ሀብታቸውን ማልማት እንዳለባቸው የመከሩት የፓርላማ አባሏ፤ የኢትዮጵያ እና የኡጋንዳ ህዝቦች በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን የበለፀገ ባህላዊ ሀብት እና እንግዳ ተቀባይነት ለኢኮኖሚ እድገት በብቃት መጠቀም በመቻሏ አድናቆታቸውን የገለፁት ደግሞ የናይጄሪያው የመረጃ ተንታኝ ፋሩክ አዲሳፌ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወጣቶች በፖለቲካውና በልማቱ ምህዳር ውስጥ የላቀ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረጋቸው አርዓያነት ያለው ስራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉ ሁለንተናዊ የልማት ምዕራፎች፣ የሰላም እና የአንድነት ጉዞዎች ለመላው አህጉሪቱ ብልፅግና ተስፋ ሰጪ ማሳያዎች መሆናቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም