ቀጥታ፡

የተሰጠን እውቅና በሽታን ቀድሞ በመከላከል ረገድ ሚናችንን ለማጠናከር ትልቅ ስንቅ ነው -የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች

ሆሳዕና፣ ጥቅምት 29/2019 (ኢዜአ)፡- በ28ኛው የጤና ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ የተሰጣቸው እውቅና በሽታን ቀድሞ በመከላከል ረገድ ያላቸውን ሚና ይበልጥ ለማሳደግ ትልቅ መነሳሳት እንደፈጠረባቸው እውቅና የተሰጣቸው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

28ኛው የጤና ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ "እመርታዊ ሪፎርም ለሉዓላዊና የማይበገር የጤና ሥርዓት!! በሚል መሪ ሀሳብ ትናንት በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።

የፌደራልና የክልል አመራሮች እና የጤና ባለሙያዎች በተገኙበት በተካሄደው በዚህ ጉባኤም ጤናማና አምራች ዜጋን ለመፍጠር በተከናወኑ ሥራዎች ጉልህ አስተዋጽዖ ላደረጉ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እውቅና ተሰጥቷል።  

እውቅና የተሰጣቸው ባለሙያዎችም ለኢዜአ እንደገለጹት፡ እውቅናው በቀጣይ በሽታን ቀድሞ የመከላከል ሥራቸውን በበለጠ ትጋት ለማከናወን መነሳሳት ፈጥሮባቸዋል።


 

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ኦሮሚያ ዞን ገመቺስ ወረዳ ኦልታኔ ቀበሌ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ የሆኑት ሀይማኖት ከተማ እንዳሉት፣ የተሰጣቸው እውቅና በሽታን ቀድሞ በመከላከል ጤናማና አምራች ዜጋን ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ሀገራዊ ጥረት ለማሳካት በበለጠ ትጋት እንዲሰሩ የሚያነሳሳ ነው።

የመጡበት አካባቢ ለወባ በሽታ ተጋላጭ መሆኑን አመልክተው፣ የወባ በሽታ በሚያሳድረው ተፅዕኖ ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት እንዲመጣ የበኩላቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የማህበረሰቡ ግንዛቤ እያደገ በመምጣቱ በአካባቢው በወባና በቲቢ በሽታዎች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መቀነሱን ገልጸው፣ "የተሰጠኝ እውቅና በጤናው ዘርፍ ለላቀ ውጤት ተግቼ እንድሰራ አነሳስቶኛል" ብለዋል።


 

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ቡልዲጉሉ ወረዳ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ የሆኑት አሻ ባበክር በበኩላቸው እንዳሉት፣ በሽታን አስቀድሞ በመከላከልና በማከም ጤናማና አምራች ዜጋን የመፍጠር ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን ሙያዊ ግዴታቸውን እየተወጡ ነው። 

ጽዱ አካባቢን ለመፍጠር እና የሕጻናት የሰውነት መቀንጨር ችግርን ለመከላከል በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ሥራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸወን ተናግረዋል።

የተሰጣቸው እውቅና በሥራቸው ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ጠንክረው እንዲሰሩ ተነሳሽነት የፈጠረባቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

በእናቶችና ሕፃናት ጤና አጠባበቅ እንዲሁም ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች መከላከያ መንገዶች ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ እያሳደጉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን መንገሺ ወረዳ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዋ መቅደስ ተክሌ ናቸው።


 

በሚሰሩበት ጤና ኬላ ለማህበረሰቡ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋና ፍትሀዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የተሰጣቸው እውቅና በዘርፉ ከሚጠበቅባቸው በላይ አስተዋጽኦ ለማድረግ ተነሳሽነት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። 

በጉባኤው ላይ እንደተገለጸው በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ አገልግሎትን በማስፋት ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብን የመፍጠር ሥራ በልዩ ትኩረት ይመራል።

ሁሉን አቀፍ የጤና ኬላዎችን ብዛት ከፍ በማድረግ እና መሰረታዊ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ጤና ጣቢያዎችን በማደራጀት በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ የተጀመሩ ተግባራትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም