ብልፅግና ፓርቲ በመደመር እሳቤ ያከናወናቸው ተግባራት ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆኑ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ፓርቲ በመደመር እሳቤ ያከናወናቸው ተግባራት ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆኑ ናቸው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29/2019 (ኢዜአ)፡-ብልፅግና ፓርቲ በመደመር እሳቤ ያከናወናቸው ተግባራት ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆኑና ትምህርት የሚቀሰምባቸው መሆናቸውን የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ገለጹ።
"ዕድገትን መምራት፤ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ትናንት ተጠናቋል።
በጉባኤው በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች በመዲናዋ የተከናወኑ የልማት ስራዎችና የተመዘገቡ ውጤቶች ጎብኝተዋል።
የካሜሩን የሶሻል ዲሞክራቲክ ፍሮንት (SDF) ሊቀ መንበርና የፓርላማ አባል ጆሹዋ ኦሲ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገራቸው ኢኮኖሚያዊ ሽግግርና ዕድገት ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡
ከፖሊሲ ቀረጻ ባሻገር ዕድገትን የሚያፋጥኑ ዋና አንቀሳቃሾች መሆን እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገራቸው የሚስማማ የልማት ሞዴል መቅረጽ እንዳለባቸው ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ የሚተገበረው የመደመር ስትራቴጂ በሀገሪቱ እየሠራ ያለውን ሥራ አድንቀዋል።
የፖለቲካ ስርዓት አካታች መሆን እንዳለበት አስገንዝበው፤ ለዚህም የመደመር መንግስት ሁነኛ ምሳሌ እንደሚሆን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤን ማስተናገዷ የብልፅግና ፓርቲ እየሠራ ያለውን ሥራ የሚያሳይ ነዉ ብለዋል።
በኢትዮጵያ በመደመር ፍልስፍና አካታች የልማት ሥራዎች እየተገነቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ዓድዋ በካሜሩን ሕዝብ ዘንድ በጥልቅ የሰረጸ ታሪክ መሆኑን ጠቁመው፤ በመታሰቢያው መገኘታቸው ኩራትና ከፍተኛ የደስታ ስሜት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ የመተላለፊያ ማዕከልነት ባሻገር የባህል፣ የፈጠራና የኢንዱስትሪ ማዕከል እየሆነች እንደምትገኝም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የመደመር እሳቤ ለአፍሪካ ሀገራት ልምድ የሚቀሰምበት እንደሆነ ገልጸዋል።
የዩጋንዳ ምርጫ ኮሚሽን ኮሚሽነር ስቲቨን ታሾቢያ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የተመዘገቡ የልማት ስኬቶች ለአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ትምህርት እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
ከዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ያዩትና አሁን የተመለከቱት የአዲስ አበባ ለውጥ እጅግ አስደናቂ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ውስጥ ያስመዘገበችው እድገት እንዲሁም ከተማዋ በመሠረተ ልማት የተለወጠችበት ሁኔታ አስደናቂ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም የብልፅግና ፓርቲ አካታችነት ትልቅ ምሳሌ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ተሞክሮ ፖለቲካ የሥልጣን መያዣ ብቻ ሳይሆን የሕዝብን ሕይወት ለማሻሻልና ለሀገር ልማት ለማገልገል የሚውል መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ሊማሩት ከሚገባ ትምህርቶች መካከል በትብብር መሥራት፣ አካታች የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር ፣ፖለቲካን ለሕዝብ ደህንነት ማሻሻያ ማዋል ዋናዎቹ እንደሆኑ አመልክተዋል።