ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስኬቶቿን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የምታካፍልበት ጉባኤ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29/2019 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስኬቶቿን እና የአፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳዎች የምታንፀባርቅበት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) በነገው ዕለት በቱርክ መካሄድ ይጀምራል።

በቱርክ አንታሊያ ከተማ የሚደረገው ይህ ጉባኤ “ከቃላት ባለፈ ወደ ተግባርና አፈጻጸም መሸጋገር” (“Where dialogue turns into global action”) በሚል መሪ ቃል እስከ ፈረንጆቹ ሕዳር 20/2026 የሚካሄድ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ረገድ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶችና የአረንጓዴ ልማት ጥረቶቿን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማካፈልና ሀገራዊ ራዕይዋን ለማንፀባረቅ ዝግጅቷን አጠናቃለች።

በአሁኑ ወቅት እንደ ከባድ ድርቅ፣ያልተጠበቀ የጎርፍ አደጋና የግብርና ምርታማነት መቀነስ ያሉ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎች የአፍሪካን የኢኮኖሚ ዕድገትና የሕዝቦቿን ሕይወት እየተፈታተኑት ይገኛሉ።

በዚህ ዳራ ውስጥ፣ ኢትዮጵያ በኮፕ 31 መድረክ ላይ የአፍሪካን ድምፅና የጋራ ፍላጎት በግንባር ቀደምትነት የምታስደምጥበት አጋጣሚ ከፍተኛ ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ ፋይዳ አለው።

ኢትዮጵያ በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባር ባሳየችው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የአህጉሩ አምባሳደር መሆኗን አስመስክራለች።

ሀገሪቱ በስፋት የምታካሂደው የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ፣ የደን ሽፋን ማሳደግ፣ የታደሰ ኃይል (የውኃ፣ የነፋስና የፀሐይ) ልማትና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ አረንጓዴ ስትራቴጂዎች በጉባኤው ላይ በጥሩ ተሞክሮነት የሚቀርቡ ናቸው።

ይህ ተግባራዊ ልምድ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምታደርገውን የሙግት አቅም የሚያጠናክር ሲሆን አፍሪካውያን ሀገራት በራሳቸው አቅምና እቅድ አየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እንደሚችሉ ማሳያ ነው።

የሰው ዘር መገኛ፣ የጽናትና የተስፋ ምድር የሆነችው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን አየር ንብረት ጉባኤ ለማስተናገድ የምታደርገውን ሀገራዊ እንቅስቃሴ በተመለከተ ሙሉና ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት፣ የጉባኤውን ትክክለኛውን የኮፕ 32 ይፋዊ ድረ-ገጽ (https://cop32ethiopia.et/) በመጎብኘት አሁናዊ መረጃዎችንና ዝግጅቶችን መከታተል ይቻላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም