ቀጥታ፡

የስኳር በሽታ ምልክቶችና መከላከያ መንገዶቹ

ጥቅምት፣ 29/2019 (ኢዜአ)፡-የስኳር በሽታ ምልክቶችና መከላከያ መንገዶቹ

የስኳር በሽታ በዓለም ላይ ስር የሰደደ የጤና ችግር እየሆነ መምጣቱን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። እ.ኤ.አ በ1980 በዓለም ላይ በስኳር በሽታ የታመሙ ታዳጊዎች ቁጥር 108 ሚሊዮን ነበር። በ2014 በከፍትኛ ሁኔታ ጨምሮ 422 ሚሊዮን ታዳጊዎች መታመማቸውን መረጃው ያመለክታል። 

የዓለም አቀፉ የስኳር በሽታ ፌዴሬሽን መረጃ እንደሚያሳያው ደግሞ በአሁኑ ወቅት በዓለም ከዘጠኝ ታዳጊዎች መካከል አንዱ የስኳር ታማሚ ይሆናል። በመሆኑም ሕጻናትና ታዳጊዎች በተለይም ለታይፕ - 2 የስኳር ሕመም አይነት በብዛት እየተጋለጡ በመሆኑ የጥንቃቄ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የዓለም ጤና ድርጅት አጽኖት ተሰጥቷል።

ለስኳር ሕመም ሳይዘናጉ የመከላከል ሥራ ትኩረት እንዲያገኝ እየተሰራ ነው። በዚህም የዘንድሮው የዓለም የስኳር ሕሙማን ቀን "Early action on diabetes" ወይም "ለስኳር ሕመም የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃ" በሚል መሪ ሃሳብ ህዳር 5 ቀን 2019 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ደረጃ ይከበራል። ዓላማውም ህብረተሰቡ ስለ ስኳር በሽታ ያለውን ግንዛቤ የማሳደግ፣ ለመከላከል የሚያስችሉ መንገዶችን የማስተዋወቅና የስኳር ታማሚዎች ተገቢውን የሕክምና እና የእንክብካቤ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ነው።

👉የስኳር በሽታ ምንድን ነው?

የስኳር በሽታ ሰውነት በቂ የኢንሱሊን ሆርሞን ማምረት ሲያቅተው ወይም የሚያመነጨውን ኢንሱሊን በአግባቡ መጠቀም ሳይችል ሲቀር የሚከሰት ሥር የሰደደ በሽታ ነው። ኢንሱሊን በቆሽት የሚመነጭ ሆርሞን ሲሆን ግሉኮስ ከደም ወደ ሰውነት ሕዋሳት በመግባት ለኃይል እንዲውል ያግዛል። ይህ ሂደት ሲዛባ የደም ስኳር መጠን ከመደበኛው በላይ ይጨምራል። ችግሩም በጊዜ ሂደት የልብ፣ የኩላሊት፣ የዓይን፣ የነርቭና የደም ሥሮችን ሊጎዳ ይችላል።

የስኳር በሽታ የተለያዩ አይነቶች አሉት። የመጀመሪያው ዓይነት-1 ወይም ታይፕ-1 የሚባል ሲሆን ሰውነት ኢንሱሊን ማምረት ሲያቆም የሚከሰት ነው። በመሆኑም የዚህ በሽታ ታማሚዎች ኢንሱሊን መውሰድ ይኖርባቸዋል ማለት ነው።

ዓይነት-2 ወይም ታይፕ-2 የሚባለው ደግሞ ሰውነት የተመረተውን ኢንሱሊን በአግባቡ መጠቀም ሲያቅተው የሚከሰት የስኳር ሕመም ነው። ሌላኛው የበሽታው አይነት በእርግዝና ወቅት የሚከሰት ሲሆን የዚህ ምክንያትም የደም ስኳር መጠን ከመደበኛው በላይ መጨመር መሆኑን የሕክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

👉የስኳር በሽታ ምልክቶች

የስኳር በሽታ ምልክቶች እንደ በሽታው ዓይነትና ደረጃ ሊለያዩ ይችላሉ። በአንዳንድ ሰዎች ላይ ምልክቶቹ በግልጽ ሳይታዩ ለረጅም ጊዜ ከበሽተኛው ጋር ሊኖሩ ይችላሉ። በተለይም ዓይነት-2 የስኳር በሽታ ቀስ በቀስ ጤናን እየጎዳ በድንገት ሊያስተኛ ይችላል። ይሁን እንጂ ሰዎች መሰረታዊ የሆኑ የስኳር በሽታ ምልክቶችን በማወቅ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ባለሙያዎች ይመክራሉ። 

የስኳር በሽታ ከሚያሳያቸው ዋና ዋና ምልክቶቹ መካከል በተደጋጋሚ ከመጠን በላይ ውሃ የመጠማት ስሜት፣ በተደጋጋሚ የሽንት መምጣት፣ በቅጽበት የሰውነት ክብደት መቀነስ፣ በቂ እንቅልፍ ቢወስዱም የድካምና የዝለት ስሜት መኖር እንዲሁም የዓይን እይታ መደብዘዝ የሚጠቀሱ ናቸው። 

በተጨማሪም የተለመደውን የምግብ መጠን ቢመገቡም የረሀብ ስሜት መጨመር፣ ቁስሎች በቀላሉ ያለመዳን፣ ተደጋጋሚ ኢንፌክሽን መከሰት፣ በእጅና በእግር የመደንዘዝና የመንዘርዘር ስሜትና ሌሎችም ይጠቀሳሉ። በመሆኑም እነዚህ ምልክቶች ሲታዩ የስኳር በሽታ አለ ብሎ በራስ መደምደም ሳይሆን ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የደም ስኳር ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል። 

👉የስኳር በሽታን እንዴት መከላከል ይቻላል?

የስኳር በሽታን ለመከላከል ከሚቻልባቸው መንገዶች መካከል ጤናማ አመጋገብ፣ ተከታታይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ የሰውነት ክብደትን ተመጣጣኝ ማድረግ እንዲሁም ትንባሆ አለማጨስ ሁነኛ መፍትሄዎቹ ናቸው። 

የስኳር በሽታ የግለሰብ የጤና ችግር ብቻ ሳይሆን የቤተሰብ፣ የማኅበረሰብና የተለያዩ ባለደርሻ አካላትን የጋራ ኃላፊነት ይጠይቃል። በመሆኑም በሽታውን በጊዜ ማወቅ፣ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት፣ ጤናማ አኗኗርን መለማመድና የሕክምና ክትትልን ማዘውተር የበሽታውን ጫና ለመቀነስ ወሳኝ ናቸው። 

ችግሩ የጋራ በመሆኑ የዓለም የስኳር ሕሙማን ቀን የሚከበረው በጋራ መከላከልን መሰረት በማድረግ ነው። በሽታውን ከመፍራት ይልቅ በትክክለኛ መረጃ ላይ በመመስረት ቀድሞ የመከላከል፣ ከመዘግየት ይልቅ በጊዜ ምርመራ የማድረግ ጉዳይ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል።

👉በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

በኢትዮጵያም የስኳር በሽታ ትኩረት የሚሻ የጤና ችግር እየሆነ መጥቷል። የዓለም አቀፉ የስኳር ሕሙማን ፌዴሬሽን መረጃ እንደሚያሳየው እ.ኤ.አ. በ2024 ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 79 ዓመት የሚገኙ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል። በመሆኑም ለስኳር በሽታ ትልቅ ትኩረት በመስጠት የመከላከል እና የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። 

በተለይም ጤናማ የሆነ የአመጋገብ ለውጥ ማድረግ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ የእግር ጉዞ ማድረግ፣ ከመጠን በላይ ውፍረትን መከላከል እና የጤና ምርመራን ልምድ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ይመክራል።

በስኳር በሽታ የተያዙ ሰዎችም በበሽታው መያዝ ማለት የሕይወት ተስፋ ማጣት ማለት ስላልሆነ ሕክምናቸውን በአግባቡ በመከታተልና የአኗኗር ዘይቤያቸውን በማስተካከል ደስተኛ ሆነው መኖር እንደሚችሉ የሕክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

በሐኪም የታዘዘውን መድኃኒት በተገቢው ሰዓትና መጠን መውሰድም ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ የደም ስኳር መጠንን መከታተል፣ ከሀኪም ምክር ውጭ መድኃኒትን አለማቆም እንዲሁም መጠኑን አለመቀነስ ወይም አለመጨመር ይገባል። በተቋማትም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ የስኳር በሽታ ያለባቸውን ሰዎች እገዛ፣ ድጋፍና እንክብካቤ ማድረግም ያስፈልጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም