ቀጥታ፡

በአፋር ክልል የተከናወኑ የውኃ ማቆር ስራዎች ውጤታማ ሆነዋል

ሠመራ፣ ጥቅምት 29/2019 (ኢዜአ)፡-በአፋር ክልል  በድርቅና በውኃ እጥረት ምክንያት በእንስሳት ላይ የሚከሰተውን ጉዳት ለመቀነስ የተከናወኑ የውኃ  ማቆር ሥራዎች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸው  ተገለጸ።

የክልሉ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከአውሮፓ ኅብረት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በቂልበቲ ረሱ ዞን ኮነባ ወረዳ ባልተማከለ የአደጋ ሥጋት አመራር ፕሮጀክት ምዕራፍ ሁለት ያስገነባቸው የውኃ ማቆርና የጎርፍ መከላከል ሥራዎች በይፋ ተመርቀዋል።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የፕሮጀክቱ የክልል አስተባባሪ አቶ ኑር መሐመድ እንደገለጹት፤ የውኃ ማቆር ፕሮጀክቱ በአርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ ዘንድ በድርቅና በውኃ እጥረት ሳቢያ በእንስሳት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ከማስቻሉም በላይ የአደጋ ሥጋትን በዘላቂነት ለመግታት ያግዛል።

ተጠናቆ ወደ ሥራ የገባው ይህ ፕሮጀክት ከ15 ሺህ 750 ሜትር ኪዩብ በላይ ውኃ የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን፥ ይህም ለእንስሳትና ለአካባቢው የመኖ ልማት ሥራዎች በመዋል ምርታማነትን ለመጨመር ከፍተኛ ሚና እንዳለው አስረድተዋል። 


 

አክለውም የውኃ ማቆር ሥራው በክረምት ወቅት የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋና የአፈር መሸርሸር ከማስቀረቱም በላይ፣ በበጋው ወቅት አርብቶ አደሩ በቅርበት ውኃ እንዲያገኝ እንደሚያስችል ጠቁመዋል። 

 5 ሺህ 850 አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው ይህ ፕሮጀክት ከአጋር አካላት ጋር በተደረገ ጥብቅ ትብብር እውን መሆኑንም አብራርተዋል።

የኮነባ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ያህያ በበኩላቸው፤ በፕሮጀክቱ የተከናወኑት ሥራዎች ለአርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ ትልቅ እፎይታ የሰጡና የአደጋ ሥጋት ተጋላጭነትን የቀነሱ ናቸው ብለዋል።

ውኃን በአንድ ቦታ በማሰባሰብ የሚከናወነው ሥራው ለእንስሳት ምርታማነትና በአካባቢው ለሚከናወኑ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚሰጥም አብራርተዋል።

ከፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች መካከል የዋህዴስ ቀበሌ ነዋሪው አቶ አሊ መሐመድ፤ የተገነባው የልማት ሥራ አካባቢውን ከሥጋት ወደ ልማት ያሻገረ መሆኑን ገልጸዋል።


 

 ግንባታው ውኃ ለማቆር ምቹ አጋጣሚ ከመፍጠሩ ባሻገር በማኅበረሰቡ ውስጥ አዲስ የልማት ተነሳሽነት መፍጠሩን አስረድተዋል። 

በዝናብ ወቅት ከከፍተኛ ቦታዎች የሚመጣውን የጎርፍ ሥጋት መቀነስ መቻሉ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረባቸው የገለጹት ደግሞ ሌላኛው ተጠቃሚ አቶ ኡስማን መሐመድ ናቸው።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አባላት፣ የወረዳው አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የልዩ ልዩ አደረጃጀት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም