መሶብ የአንድ ማዕከል ፈጣንና የተሻለ አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል -ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል ፈጣንና የተሻለ አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል -ነዋሪዎች
አምቦ፣ ጥቅምት 29/2019 (ኢዜአ)፡-መሶብ የአንድ ማዕከል ፈጣንና የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው በማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን የጉደር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግሥት አሰራርን ለማዘመን፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትና የሕዝቡን እርካታ ለማሳደግ ታስቦ ከተዘረጉ ዋና ዋና የህዝብ አገልግሎት ማሻሻያ ተቋማት አንዱ ነው፡፡
ማዕከሉ በኦሮሚያ ክልል በስፋት እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን፤ በማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን ጉደር ከተማም የህዝቡን እንግልት በማስቀረት ረገድ አዎንታዊ ውጤት እያመጣ ይገኛል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪዎች በአንድ ቦታ የተሟላ፤ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘታቸው ከዚህ በፊት የተለያዩ ቦታዎች ሄደው ይባክን የነበረውን ጊዜ እና ጉልበታቸውን እንዳስቀረላቸው ገልጸዋል፡፡
በማዕከሉ የሥራ ፍቃድ ለማውጣት የመጡት አቶ ፈይሳ ሞሲሳ እንዳሉት፤ ቀደም ሲል አንድ ጉዳይ ለማስጨረስ ከሁለት ሳምንት እስከ አንድ ወር እንደሚመላለሱ አስታውሰው አሁን ላይ ባጠረ ጊዜ ውስጥ የሚፈልጉትን ፈጽመው ለመመለስ ችለዋል፡፡
መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረውን ረጅም ወረፋ ከማስቀረት ባለፈ የተገልጋይን እንግልትና የሚባክን ጊዜ ማስቀረቱን ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ መሐመድ ከድር የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር ለማግኘት ወደ ማዕከሉ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
ማዕከሉ ፈጣንና ተደራሽ አገልግሎት በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ስለሚሰጥ በፊት ይታዩ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እያቃለለ ለማህበረሰቡ አስፈላጊ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ ለመገልገል መምጣቱን በመጥቀስ ዛሬ የመጣበትን የገቢ ግብር ጉዳይ በ10 ደቂቃ መጨረሱን የተናገረው ደግሞ ወጣት ጉደታ ተሬሳ ነው፡፡
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በቅርበትና በፍጥነት ማግኘቱ ጊዜና ገንዘብ እንደቆጠበለት በመግለጽ በአገልግሎቱ መደሰቱን ተናግሯል፡፡
የጉደር ከተማ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ ኤልያስ ሂርጳሳ በበኩላቸው፤ ከዚህ በፊት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይነሳ የነበረው የሕዝብ ቅሬታ ማዕከሉ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ መቀረፉን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ማዕከሉ ዘጠኝ የከተማው ሴክተር ጽህፈት ቤቶችን 54 አገልግሎቶችን በተሟላ መልኩ እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
ማዕከሉ ከሐምሌ 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ አንስቶ ከ 5 ሺህ 600 በላይ የከተማው ነዋሪዎችን በማስተናገድ ፈጣንና ተደራሽ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ከማዕከሉ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡