ቀጥታ፡

የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ጥቅምት 29/ 2019(ኢዜአ):-የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

መስተዳድር ምክር ቤቱ በዋናነትም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ከሁለት ቢሊዮን ስድስት መቶ ሀምሳ ስድስት ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ለ16 አልሚዎች በክልሉ እንዲያለሙ የመስሪያ ቦታ በምደባ እንዲሰጥ ውሳኔ አስተላልፏል።

የመስሪያ ቦታ እንዲሰጥ ውሳኔ የተላለፈውም በልዩ ሀገራዊና ክልላዊ ፋይዳ ባላቸው በተለይ በሆቴልና ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪና ማኑፋክቸሪንግ፣ የእርሻና ምርት ማቀነባበሪያ፣በቅይጥ አገልግሎትና በሆስፒታል እንዲሁም ለመዝናኛ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ነው።

የመሬት ምደባ የተደረገላቸው ባለሐብቶች በሚሰማሩበት የልማት መስክም ሀገራዊና ክልላዊ ፋይዳ ያላቸውና ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስለመሆናቸው ተጠቁሟል።


 

መስተዳድር ምክር ቤቱም ለባለመብቶቹ የተሰጠው መሬት ለተፈለገው ልማት በማዋል በአፋጣኝ ወደ ስራ እንዲገቡ አቅጣጫ አስቀምጧል።

በአጀንዳው ጥልቅ ውይይት ያካሔደው መስተዳድር ምክር ቤቱ ውሳኔውን በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።

የክልሉ መንግስት የኢንቨስትመንት ዘርፉን የበለጠ ለማነቃቃት በትኩረት እየሰራ መሆኑም ተመላክቷል።

በቀጣይም ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸውና የህዝብን ተጠቃሚነት በሚያጎለብቱ ዘርፎች ላይ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል።

መስተዳድር ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪም በሌሎች አጀንዳዎች ዙሪያ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም