ቀጥታ፡

ለሕብረተሰብ ጤና ስጋት የሚሆኑ ወረርሽኞችን መከላከል የሚያስችል አቅም ተገንብቷል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29/2019 (ኢዜአ)፡-ለሕብረተሰብ ጤና ስጋት የሚሆኑ ወረርሽኞችን መከላከል የሚያስችል አቅም መገንባቱን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጤናው ዘርፍ መሰረተ ልማትን ከማስፋፋት ጀምሮ የህብረተሰቡን ተደራሽነት ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል።

በዚህም የጤና ተቋማት እና አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋፋት የእናቶችና ህጻናት ጤናን ያሻሻሉ እና ለህብረተሰብ ጤና ስጋት የሚሆኑ ወረርሽኞችን አስቀድሞ የመከላከል አቅምን የሚያሳድጉ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። 

በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ዝግጁነት ዳይሬክተር ነኢማ ዘይኑ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ወረርሽኞች መከሰታቸውን አስታውሰዋል።


 

ሀገሪቱም በጤናው ዘርፍ ስጋት የሚሆኑ ወረርሽኞች በሚከሰቱበት ወቅት አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ረገድ፣ እንዲሁም በሽታዎች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድሞ መከላከል ላይ በምትሰራቸው ልዩ ልዩ ተግባራት አበረታች ውጤቶችን አስመዝግባለች ብለዋል።

በተለይም ከወረርሽኝ ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ በሽታዎችን ለመከላከል በሀገሪቱ ብቁ የሰው ሀይል ከማፍራት፣ የላብራቶሪ አቅምን ከማሳደግ እና የተቋማትን አቅም ለማጠናከር የሚሰሩ ስራዎች ሀገሪቱ ለከፋ የወረርሽኝ አደጋ ተጋላጭ እንዳትሆን አስችሏታል ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ ሲከሰት በሽታውን በአጭር ጊዜ መከላከል መቻላችን፣ ሀገሪቱ ወረርሽኝን ለመግታት የገነባችውን ጠንካራ አቅም የሚያረጋግጥ አንዱ ማሳያ ነው ሲሉ አንስተዋል።

ከዚህም ባለፈ የኢትዮጵያ የድንገተኛ ህክምና ቡድን በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የማግኘቱ ምክንያት፣ ድንገተኛ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ በገነባው አቅም እንደሆነም አብራርተዋል።

ኢንስቲትዩቱም በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ወረርሽኞችን አስቀድሞ ለመከላከልና ከተከሰቱም አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ጠንካራ አቅም የመገንባት ስራ ቀጣይነት ባለው መልኩ እያከናወነ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ በተወሰኑ ሀገራት ላይ ከተከሰተው የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተገናኘ ሀገራችን የበሽታው ተጋላጭ እንዳትሆን አስቀድሞ የዝግጁነት አቅም መገንባት ላይ ትኩረት ተደርጎ በፌደራልም በክልሎችም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ኢንስቲትዩቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የባለሙያዎችን አቅም የመገንባት፣ የሰው ኃይልና ግብዓት የማሟላት እንዲሁም በህክምና ተቋማት ለይቶ ማቆያዎችን የማዘጋጀት ቅድመ ጥንቃቄዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ወረርሽኝን ለመከላከል የሚሰሩ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ በተለይም በሽታው ከተስተዋለባቸው ሀገራት በተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮች የሚመጡ መንገደኞችን ምርመራ የማድረግ ስራ በፌደራል እና በክልል ደረጃ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

ምርመራ ተደርጎላቸው ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ መንገደኞችንም ለተከታታይ 21 ቀናት ተጨማሪ ክትትል የሚደረግበት የአሰራር ሁኔታ መመቻቸቱንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም