ቀጥታ፡

የሳምንቱ ተጠባቂ መርሐ ግብር ፣ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2019 (ኢዜአ)፦  በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛ ሳምንት ስድስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ከቀኑ 10 ሰዓት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚያከናውኑት ጨዋታ ትኩረትን ስቧል።

የወቅቱ ሻምፒዮን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስድስት ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአራት ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ይዟል።

ሁለቱ ክለቦች በ2018 ዓ.ም የውድድር ዓመት ዋንጫውን ለማንሳት ያደረጉት ጠንካራ ፉክክር አጓጊ የሚባል ነበር።

በመጨረሻ ሳምንት (25ኛ ሳምንት)  ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2 ለ 0 አሸንፏል።

እሙሽ ዳንኤል እና ረድኤት አስረሳኸኝ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ69 ነጥብ ሻምፒዮን ሆኗል።  እስከ መጨረሻው ለዋንጫ የተፎካከረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ66 ነጥብ ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል።

ሁለቱ ቡድኖች በጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሌሎች መርሐ ግብሮች ልደታ ክፍለ ከተማ ከሸገር ከተማ ከረፋዱ አራት ሰዓት፣ መቻል ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ ስምንት ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ሀዋሳ ከተማ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

አዳማ ከተማ ከጉለሌ ክፍለ ከተማ በወንጂ ስታዲየም እና ጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማዕከል ከባህር ዳር ከተማ በማዕከሉ ሜዳ በተመሳሳይ 9 ሰዓት ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም