የአፍሪካ የልማት ተምሳሌቷ፡ዘላቂ መሠረተ ልማት እመርታ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ የልማት ተምሳሌቷ፡ዘላቂ መሠረተ ልማት እመርታ
አዲስ አበባ በለውጥ ጉዞዋ ውስጥ የጀመረችውን የከተማ ልማት እንቅስቃሴ ግለት ሳታስቀይር፣ የዘላቂ መሠረተ ልማት ግንባታዋን በማፋጠን ወደ ተቀናጀና ዘመናዊ ከተማነት እየተጓዘች ትገኛለች።
የሦስተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ይህንኑ የለውጥ ጉዞ በግልጽ የሚያሳይ ተግባራዊ እመርታ ነው።
ከጎሮ–ኮዬ ፈጬ እስከ ቱሉ ዲምቱ የሚዘልቀው 15 ኪ.ሜ. ርዝመትና 114 ሜትር ስፋት ያለው የመንገድ ልማት፣ ሰፋፊ የእግረኛና የሳይክል መንገዶች፣ 70 ሄክታር የመንገድ ዳር አረንጓዴ ልማት እንዲሁም የውኃና የፍሳሽ መሠረተ ልማቶች የዚህ ጥምር ልማት አካል ናቸው።
በተመሳሳይ ከካራ–ቦሌ አየር ማረፊያ መንገድ በጎሮ እስከ አቃቂ የሚዘልቀው 22 ኪ.ሜ. የወንዝ ዳርቻ ልማት 324 ሄክታር መሬትን በሚሸፍን የአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት፣ በጋቢዮንና በእርከን ሥራዎች እየተፋጠነ ይገኛል።
እነዚህ ሥራዎች የመንገድ ግንባታ ብቻ ሳይሆኑ የከተማዋን የኑሮ ጥራት ለማሻሻል፣ የአካባቢ ጥበቃን ለማጠናከር፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ለማስፋፋትና ለቀጣይ ትውልድ የሚበቃ ዘላቂ የከተማ አካባቢ ለመፍጠር የታለሙ ናቸው።
የለውጥ ጉዞ በአንድ ወቅት ተጀምሮ የሚቆም ሳይሆን በቀጣይነት በትጋትና በቁርጠኝነት የሚገነባ ነው። አዲስ አበባም የጀመረችውን የልማት እመርታ በማስቀጠል በሌት ተቀን እየሠራች ትገኛለች።
የከተማ ልማት በቅንጅት የሚሰራ ፤ በተደመረ አቅም ሁሉም ባለበት ባለው አቅም በመንቀሳቀስ የሚሳካ የልማት ስራ ነው። በአካባቢው ቅድሚያ የማልማት መብት ያገኛችሁ የግል አልሚዎችም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ እና ከከተማዋ የልማት እመርታ ጋር በመሄድ የልማት ሥራቸውን እንዲያፋጥኑ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አሳስበዋል።