ቀጥታ፡

የአትሌቲኮ ማድሪድ እና ባርሴሎና የላሊጋ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29/2019 (ኢዜአ)፡- በስፔን ላሊጋ የ12ኛ ሳምንት መርሐ ግብር አትሌቲኮ ማድሪድ እና ባርሴሎና ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ትኩረት ስቧል።

ጨዋታው ምሽት አምስት ሰዓት ላይ 70 ሺህ 692 ተመልካች በሚያስተናግደው ዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም ይካሄዳል።

አትሌቲኮ ማድሪድ በሊጉ እስከ አሁን ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች በዘጠኙ ድል ሲቀናው አንድ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪው ጨዋታ አቻ ተለያይቷል።

በጨዋታዎቹ ላይ 22 ግቦችን ሲያስቆጥር 8 ጎሎችን አስተናግዷል። የማድሪዱ ክለብ በ28 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው ባርሴሎና በበኩሉ 11 ጨዋታዎችን አከናውኖ በ10ሩ አሸንፎ በአንዱ ሽንፈት አስተናግዷል።

46  ጎሎችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 12 ግቦች ተቆጥረውበታል። የካታላኑ ክለብ በ30 ነጥብ ሊጉን እየመራ ይገኛል።

ሁለቱ ክለቦች በሁሉም ውድድሮች ሲገናኙ የዛሬው ለ255ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ በፊት ባደረጓቸው 254 የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ባርሴሎና 116 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል።

አትሌቲኮ ማድሪድ 81 ጊዜ ድል ቀንቶታል። 57 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

በላሊጋው እስከ አሁን 178 ጊዜ ተገናኝተው ባርሴሎና 83 ጊዜ አሸንፏል። አትሌቲኮ ማድሪድ 53 ጊዜ ሲያሸንፍ 42 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

ባርሴሎና ድል ከቀናው የሊጉን መሪነት ያጠናክራል። አትሌቲኮ ማድሪድ ባርሴሎናን በልጦ የሊጉ አናት ላይ ለመቀመጥ ይፋለማል።

ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም