የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተጠባቂ መርሐ ግብሮች - ኢዜአ አማርኛ
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተጠባቂ መርሐ ግብሮች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2019 (ኢዜአ)፦ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል።
በዕለቱ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ ማንችስተር ዩናይትድ ከአስቶንቪላ በኦልድትራፎርድ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ባለሜዳው ማንችስተር ዩናይትድ በሰባት ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ቡድኑ ወራጅ ቀጠና ሲገባ ከእ.አ.አ 1986/87 የውድድር ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
አስቶንቪላ በ12 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ዩናይትድ ባለፉት ሰባት የሊግ ጨዋታዎች ከድል ርቋል። ቡድኑ ከውጤት ማጣት ቀውስ እና ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ዛሬ ማሸነፍ ይኖርበታል።
በዘጠነኛ ሳምንት ከፉልሃም ጋር አንድ አቻ የተለያየው አስቶንቪላ የድል መንገዱን ለማግኘት ይጫወታል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ሰንደርላንድ ከቼልሲ ከቀኑ 11 ሰዓት በስታዲየም ኦፍ ላይት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሰንደርላንድ በአምስት ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃ ይዟል።
ባለፉት ሰባት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።
ተጋጣሚው ቼልሲ በ16 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል። በዘጠነኛ ሳምንት ማንችስተር ዩናይትድ 2 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።
ጨዋታው ሰንደርላንድ ከውጤት ቀውሱ ለመውጣት፣ ቼልሲ በድል ጉዞ ለመቀጠል የሚያደርጉት ነው።
ክሪስታል ፓላስ ከሊቨርፑል ከቀኑ 11 ሰዓት በሰልኸረስት ፓርክ የሚያደርጉት ጨዋታ ሌላኛው የዕለቱ መርሐ ግብር ነው።
ባለሜዳው ክሪስታል ፓላስ በሰባት ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ሊቨርፑል በ15 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ፓላስ ባለፉት ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል።
ተጋጣሚው ሊቨርፑልም በዘጠነኛ ሳምንት በአርሰናል 1 ለ 0 ተሸንፏል። ጨዋታው ሁለቱ ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።
ከቀኑ 11 ላይ ብራይተን ከብሬንትፎርድ በአሜክስ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
በጠንካራ ግስጋሴ ላይ የሚገኘው ብራይተን በ19 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። ብሬንትፎርድ በ14 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በዘጠነኛ ሳምንት ብራይተን ማንችስተር ሲቲን 1 ለ 0፣ ብሬንትፎርድ ኖቲንግሃም ፎረስትን 2 ለ 0 አሸንፈዋል።
ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል የሚል ሰፊ ግምት አግኝቷል።