ቀጥታ፡

የከተማ ግብርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የገቢ አቅምን ለማሳደግና የስራ እድልን ለመፍጠር እያገዘ ነው

አዋሽ መልካሣ ፣ጥቅምት 28/2019(ኢዜአ )፡- የከተማ ግብርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የገቢ አቅምን ለማሳደግና የስራ እድልን ለመፍጠር እያገዘ መሆኑ ተገለጸ።

በአዋሽ መልካሣ ወረዳ ፓፓያን በክላስተር ያለሙ አርሶ አደሮች በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር ምርቱን ለውጭና ለሀገር ውስጥ ገበያ አቅራቢዎች በማሳቸው ላይ ማስረከብ ጀምረዋል።


 

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በወቅቱ እንደገለፁት  የከተማ ግብርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የገቢ አቅምን ለማሳደግና የስራ እድል ለመፍጠር እያገዘ ነው።

አርሶ አደሩ በተለይም በመስኖ በመታገዝ የተለያዩ ሰብሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተማዋ ለመስኖ አመቺ የሆነ 17 ሺህ ሄክታር መሬት መኖሩን ጠቁመው አርሶ አደሩ ያለውን አመቺ አቅም በመጠቀም የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥና ኑሮውን እንዲያሻሽል እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የግብርናውን አሰራር ለማዘመን መስኖን ከማስፋፋት ጎን ለጎን ሜካናይዜሽንና ቴክኖሎጂ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን አክለዋል።

በዛሬው እለት ለምርት የበቃ ፓፓያ እየተሰበሰበና ለገበያ እየቀረበ መሆኑን ጠቁመው በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር መፈጠሩን ተናግረዋል።

የተፈጠረው የገበያ ትስስር አርሶአደሩን ከግብርና ምርት ላኪዎችና አከፋፋዮች ጋር በቀጥታ በማገናኘት የጋራ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ያለመ መሆኑንም ገልጿል ።

በዚህም የህገ ወጥ ደላሎችን ጣልቃ ገብነትን በማስወገድና አርሶአደሩ ለምርቱ የተሻለ ዋጋ አግኝቶ የተሻለ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ እንዲሆን ነው ብለዋል።


 

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አለሙ ደሳ (ዶ/ር) እንደገለፁት መሬትና የሰው ጉልበትን አቀናጅቶ በመጠቀም የብልጽግና ጉዞን ማረጋገጥ አለብን ብለዋል።

የአዳማ ከተማ አርሶአደሮች ከተፈጥሮ ዝናብ በመላቀቅ በሜካናይዜሽን በመጠቀም በስፋት በመስኖ መሳተፍ አለባችሁ ሲሉ አሳስበዋል ።

ቢሮው የአርሶአደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በጥናትና ምርምር የታገዘ የመስኖ ልማት ስራዎች በስፋት ለማከናወን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል ።


 

የአዳማ ከተማ ግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለሙ ቂልጡ በበኩላቸው በከተማዋ በተለይ የዝናብ እጥረት በሚታይባቸው አከባቢዎች በመስኖ ስንዴና ፍራፍሬ እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ስንዴ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ፣ ብርትኳንና ሎሚ በክላስተር እየለማ ይገኛል ነው ብለዋል።

አስተዳደሩ 22 የእርሻ ትራክተሮችን በመግዛት ለአርሶአደሩ መስጠቱንም አስታውቀዋል።


 

በዘርፉ ከተሰማሩ አርሶአደሮች መካከል ቦሩ ቁምቢ  በሰጡት አስተያየት በአሁኑ ወቅት መስኖን በመጠቀም ስንዴ፣ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የገበያ ትስስር ተፈጥሮልን በማሳችን ላይ ምርቱን ለገበያ እያቀረብን እንገኛለን ሲሉም አክለዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም