በሲዳማ ክልል የፍትህ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ በማገዝ የማህበረሰቡን እርካታ የማሳደግ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የፍትህ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ በማገዝ የማህበረሰቡን እርካታ የማሳደግ ተግባራት ይጠናከራሉ
ሀዋሳ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ) :- በሲዳማ ክልል የፍትህ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ በማገዝ የማህበረሰቡን እርካታ የማሳደግ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ ።
ቢሮው የ2019 በጀት ዓመት እቅድና የበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ ላይ ያተኮረ የሴክተር ጉባኤ በይርጋለም ከተማ አካሂዷል።
የቢሮው ሃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ፈቃዱ ጳውሎስ በወቅቱ እንደተናገሩት፣ ክልል የፍትህ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ በማገዝ የማህበረሰቡን እርካታ የማሳደግ ተግባራት ይጠናከራሉ።
በተያዘው በጀት ዓመትም ተቋማትን ሪፎርም በማድረግ የተገልጋዩን ጊዜና ጉልበት የሚቆጥቡ፣ የሀሰት ሪፖርቶችንና የመረጃዎች መጥፋትን የሚያስቀሩ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን የማስፋትና የማደራጀት ስራ በትኩረት ይከናወናል ብለዋል።
በማህበረሰቡ ዘንድ የላቀ ተቀባይነት ያለውና ዘላቂ ፍትህን በመስጠት ውጤታማ የሆነው የሲዳማ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት “አፊኒ ሶንጎ”ን የማጠናከር ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ደምሴ ዱሌቻ በበኩላቸው፣ እንደ ክልል የተቀላጠፈ ፍትህን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችን በቴክኖሎጂ የማስደገፍ ጥረት ውጤት እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በሁሉም ወረዳዎች የሚሰጡ ተዘዋዋሪ ችሎቶች የፍርድ ሂደትና ክርክር በቪዲዮ ኮንፈረንስ መካሄዱ ቀልጣፋ የፍትህ ስርዓትን ለማስፈን እያስቻለ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ባለፈው በጀት ዓመት ከ45 ሺህ በላይ መዝገቦች ውሳኔ የተሰጠባቸው መሆኑን አንስተው፣ በቀጣይም የማህበረሰቡን የፍትህ ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እንደሚከናወኑም አንስተዋል።
በመድረኩ ከተሳተፉት የሲዳማ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የወንጀልና የትራፊክ አደጋ ምርመራ ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ሀይሳ ዓለሙ በበኩላቸው፣ ወንጀልን ለመከላከልና ቀልጣፋ የፍትህ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ ነው ብለዋል።
በሲዳማ ክልል ምክር ቤት የህግ፣ የፍትህና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አማኑኤል መንግስቱ፣ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የፍትህ ጥያቄዎች ለማጣራት የመስክ ምልከታ መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህም የፍትህ ሴክተር እየሰራ ያለውን በመገምገም የህዝብን የፍትህ ጥያቄ ቀልጣፋ በሆነ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ እንዲቻል፣ የፍትህ ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት ክትትል የማድረግ ስራ እንደሚጠናከርም አረጋግጠዋል።