ሰላምን ለማጠናከር ከሃይማኖት ተቋማት ጋር የተፈጠረው አብሮ የመስራት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምን ለማጠናከር ከሃይማኖት ተቋማት ጋር የተፈጠረው አብሮ የመስራት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 28/2019 (ኢዜአ) ፦ ሰላምን ለማጠናከር ከሃይማኖት ተቋማት ጋር የተፈጠረው አብሮ የመስራት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የሰላም ሚኒስትር አቶ ሙሳ አደም ገለጹ።
ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እና ከቤተክርስቲያኗ ብፁዓን አባቶች ጋር ትውውቅ አደርገዋል።
በዚህ ወቅት ሚኒስትሩ እንዳሉት የሰላም ሚኒስቴር በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር የጀመረውን ገንቢ ግንኙነት አጠናክሮ ይቀጥላል።
የመደመር መንግስት የቤተክርስቲያኒቱ ታሪክ እንዲጠበቅ እና ተቋማዊ አቅሟ እንዲጠናከር ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በበኩላቸው ቤተክርስቲያኒቷ ሀገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥና ምዕመኖቿ በሰላም የሰርክ ተግባራቸውን እንዲያከውኑ እየሰራች መሆኑን ገልፀው ይኸው ተግባሯ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
በሰላም ሚኒስቴር የግጭት አፈታትና የሰላም ግንባታ ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በበኩላቸው የመደመር መንግስት ቤተክርስቲያኒቱ በሀገር ግንባታ ሂደት ከሌሎች የሀገሪቱ ሃይማኖቶች ጋር በመሆን የተጫወተችውን ሚና በሚገባ እንደሚገነዘብ ገልፀዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ዘላቂ እና አዎንታዊ ሰላምን ለማረጋገጥ ከቤተክርስቲያኒቱ ጋር የተጀመሩ ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በትውውቅ መርሃ- ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሪዮስ እና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ተገኝተዋል።